AMN – ግንቦት 09/2018 ዓ.ም
የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲን አለም አቀፍ ተነባቢ በሆነው ቢዝነስ ትራቭለር መጽሔት ገጸ-ድር ላይ አዲስ አበባ እያካሄደች ያለቸውን አካታች ልማት በሚመለከት ሐሳባቸውን አጋርተዋል።
በጽሑፋቸው የአዲስ አበባ የከተማ ልማት ሥራ ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ አዲስ ቅርጽና ዘመናዊ የከተሜነት መልክ እየሰጣት መሆኑንና አጠቃላይ የነዋሪዎችን ሕይወት እያሻሻለ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
ቀደም ሲል በተሽከርካሪ መጨናነቅ እና በጠበቡ መንገዶቿ የምትታወቀው አዲስ አበባ በኮሪደር ልማቱ ሰፋፊ ጎዳናዎችን ከአረንጓዴ ሥፍራዎች ጋር በማቀናጀት ወደ ዓለምአቀፍ ከተማነት እየተቀየረች መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ አቶ ዘመን ገለጻ በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው ግንባታ መሰረተ ልማት ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን ማህበራዊ ፍትህን የልማቱ ማዕከል ያደረገ ሰው ተኮርነቱንም በተግባር ያረጋገጠ ነው።
የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቱ የአዲስ አበባን መንገዶች በማዘመን ሳያቆም ለንግድ እንቅስቃሴዋም ምቹ መደላድል የፈጠረ መሆኑን ነው አቶ ዘመን ቢዝነስ ትራቭለር መጽሔት ላይ ያሰፈሩት።
በኮሪደር ልማት ፕሮጀክቱ ከ5ሺ 900 በላይ ነባር እና አዳዲስ ሱቆች እድሳትና ግንባታ ተከናውኗል።

በኩሪደር ልማቱ የተገነቡት ሱቆች ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሥራ ዕድልን መፍጠራቸውንና ምቹ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር ያስችሉ መሆናቸውን ነው አቶ ዘመን የጠቀሱት፡፡
የአዲስ አበባ ወንዝ ዳርቻዎች ልማት በአንድ ወቅት የቆሻሻ መከማቻና የበሽታ ምንጭ የነበሩ አካባቢዎችን ወደ አስደናቂ የጎብኚዎች መዳረሻነት እና የነዋሪዎች ማረፊያነት መቀየራቸውንም ገልጸዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ የፖለቲካ መናገሻ እና የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደመሆኗ ይህን ደረጃዋን የሚመጥን የከተማ መሠረተ ልማት መዘርጋቷን የጠቀሱት አቶ ዘመን ፣ ቀዳሚ የዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ማዕከል የመሆን ጉዞዋን እንደሚያጠናክረው አብራርተዋል፡፡

የልማቱ ትልቁ ስኬት ሁሉንም የመዲናዋን ነዋሪ ያካተተ መሆኑ ነው ያሉት አቶ ዘመን ፣ የልማት ቱርፋቱ እያንዳንዱን ዜጋ ተጠቃሚ ማድረጉን ማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራበት ገልጸዋል፡፡
የተከናወነው የኮሪደር ልማት ለተሽከርካሪ ብቻ ሳይሆን ለእግረኛ ቅድሚያ በመስጠት ሰፋፊና ደረጃቸውን የጠበቁ መንሸራሸሪያዎች ከአስፋልት መንገዱ እኩል መግንባታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
መዲናዋ ሁሉም ዜጋ ሊገለገልባቸው የሚችልባቸው ፓርኮች ፣ መናፈሻዎች እና የስፖርት ማዘውተሪያዎች በመገንባት ለነዋሪዎቿ እኩል የመዝናኛ ዕድል መፍጠሯንም አክለዋል፡፡
የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን ወደ ጽዱና ጤናማ መኖሪያዎች በመቀየር ለሰው የሚገባውን ክብር ያለው ሕይወት ማጎናጸፍ ያስቻሉ የልማት ፕሮጀክቶች መሆናቸውንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ከግንባታ ፕሮጀክቶች የዘለለ የታሪካዊ ቅርስነት ፋይዳ እንደላቸው የጠቀሱት የኤ.ኤም.ኤን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲን ፣ አዲስ አበባ ወደ ዘመናዊ ከተማነት በምታደርገው ግስጋሴ ሁሉንም ነዋሪ ተጠቃሚ እያደረገች አቅፋ መጓዟን መረጋገጫ ናቸው ብለዋል፡፡
በታደሰ ሽፈራው