AMN – ግንቦት 9/ 2018 ዓ.ም
ኢንስቲትዩቱ ከሰኔ 2018 እስከ መስከረም 2019 ዓ.ም ድረስ ያለውን የክረምት ወቅት ለሰሜን፣ ሰሜን ምስራቅ፣ መካከለኛው፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ምዕራብ እና ምስራቅ የሀገራችን አከባቢዎች ዋነኛ የዝናብ ወቅት መሆኑንና ከዓመታዊ የዝናብ ድርሻም እስከ 85 በመቶ የሚሆነውን እንደሚሸፍን ገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት የትሮፒካል ፓስፊክ እና የሰሜናዊ ህንድ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት መደበኛ ቢሆንም፤ ከሐምሌ ጀምሮ ግን የፓስፊክ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት የመሞቅ አዝማሚያ ሊያሳይ እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በዚህም መሠረት መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ፡ የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች እንደሚያገኙ አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል በደቡብና ምስራቅ ትግራይ፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ የአፋር ክልል ዞኖች፣ ምስራቅ የሀገራችን አካባቢዎች፣ እንዲሁም መካከለኛውና ደቡብ ኦሮሚያ መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ ኢንስቲትዩቱ በትንበያ መረጃው ጠቁሟል፡፡
የመካከለኛውና የምዕራብ ትግራይ እንዲሁም ምዕራብ አማራ ዞኖች ደግሞ መደበኛና በጥቂት ስፍራዎች ከመደበኛ በታች ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

በደቡብ ምዕራብና ምዕራብ አካባቢዎች ዝናቡ ቀድሞ የሚጀምር ሲሆን፤ አወጣጡ ግን ከአብዛኛው አካባቢዎች ቀድሞ እንደሚወጣና በደቡብና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ደግሞ ሊዘገይ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
ይህ በመሆኑም ለግብርና ስራዎችና ለማሳ ዝግጅት፤ ለመስኖና ለተለያዩ የልማት ስራዎች በቂ ውሃ ለማግኘት፤ ለግድቦችና ተፋሰሶች የውሃ ሙላትና ለኃይል አቅርቦት፤ ለአካባቢ ጥበቃና ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ጠቀሜታ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ ያመላክታል፡፡
በእነዚህ ወራት በሰሜን፣ ሰሜን ምስራቅ፣ መካከለኛውና ምስራቅ አካባቢዎች የሚከሰቱ ደረቅ ቀናትና የዝናብ መዋዥቅ፤ በደቡብ ምዕራብና ምዕራብ አካባቢዎች የሚከሰት ቅጽበታዊ ጎርፍና የወንዞች ሙላት፤ በማሳዎች ላይ የውሃ መተኛትና የእርጥበት መብዛት፤ በተለያዩ አካባቢዎች ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችልም ኢንስቲትዩቱ ጠቁሟል፡፡
ስለዚህ የሚገኘውን ዝናብ በአግባቡ ማጠራቀም፣ በከተሞችና በገጠር የውሃ ማፋሰሻና መቀልበሻ ቦዮችን ማዘጋጀትና ማጽዳት፣ በጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እና ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ ነገሮችን ማጽዳት እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል፡፡
See less