AMN- ግንቦት 9/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ እያከናወነች ያለውን መጠነ ሰፊ የልማት ስራ ለማስቀጠል ህዝብን መሰረት ያደረገ የሰላምና ደህንነት ኃይል መገንባት የላቀ ሚና እንዳለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የ2018 ዓ.ም 7ኛ ዙር አዳዲስ ምልምል የሰላም ሰራዊት አባላትን አስመርቋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ ህዝብን ማእከል ያረገደ የሰላምና ጸጥታ ተቋም መመስረት ይገባል ብለዋል።

በተለይም አዲስ አበባ በዓለም አደባባይ አድናቆትን ያተረፉ የልማት ስራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ ገልጸው፣ እነዚህን የልማት ስራዎች ለማስቀጠል ህዝባዊ የሰላምና ጸጥታ አደረጃጀቶች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።
ህዝባዊ አደረጃጀቶችን በመፍጠርና ከጸጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የመዲናዋን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ማስፈን ተችሏል ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው፣ ዛሬ የተመረቁት ከ12ሺ ባላይ የሰላም ሰራዊት አባለት ተደማሪ ኃይል ናቸው ብለዋል።
በማይቋረጠው የአዲስ አበባ ሁለንተናዊ እድገት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠንካራ የሰላምና ደህንነት ስራ እየተሰራ ነው ያሉት ኃላፊዋ በተለይ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሰላም ሰራዊት ሚና የላቀ ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮ ማቲያስ በሰጡት የስራ መመሪያ ተመራቂ የሰላም ሰራዊት አባላት ከነባሮች ጋር በመቀናጀት የመዲናዋን ሰላም ከማስጠበቅ ባሻገር 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በሔኖክ ዘነበ