የአራዳዋ ትንሿ ከተማ – የልጆች ዓለም

You are currently viewing የአራዳዋ ትንሿ ከተማ – የልጆች ዓለም

AMN- ግንቦት 11/ 2018 ዓ.ም

በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ማራኪው የአራዳ ፓርክ ፣ በውስጡ በርካታ ድንቅ የፈጠራ ሥራዎችን አቅፎ ይዟል። ከእነዚህ አስደናቂ ስፍራዎች መካከል ደግሞ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበና አድናቆትን እያተረፈ የሚገኘው፣ ለሕጻናት ተብሎ የተዘጋጀው “ትንሿ ከተማ” የተሰኘው የልጆች ዓለም ነው።

ትንሿ ከተማ ነባራዊውን እውነተኛ ዓለም በሕጻናት ልክ አሳንሶ የሠራ ድንቅ የዕውቀትና የፈጠራ አውድ ነው። አንድ ከተማ ሊኖሩት የሚገቡ ማኅበራዊና ተቋማዊ አደረጃጀቶችን ሁሉ አካቶ በተገቢው ጥንቃቄ ነው የተገነባው።

በማዕከሉ ውስጥ የሚገኙት ካፌዎች ፣ ቲያትር ቤቶች፣ ባንኮች፣ የፖሊስ ጣቢያ፣ ጂምናዚየም ፣ የጸጉር መዋቢያ ሳሎን፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የገበያ ቦታዎች፣ የከብቶች ጉሮኖ፣ እንዲሁም ተሽከርካሪዎችና የእግረኛ መሻገሪያዎች የዚሁ እውነተኛ መልክ ነጸብራቅ ናቸው።

ማዕከሉ ሕጻናት የዛሬው ዘመን ትልቅ አደጋ ከሆነው የዲጂታል ስክሪን ነፃ ሆነው፣ የእውነተኛውን ዓለም ማኅበራዊ አኗኗር፣ ሥርዓትና የዕለት ተዕለት መስተጋብር በተግባር እንዲለማመዱ ዕድል ፈጥሯል።

ሁላችንም የምናውቀውን የልጅነት የ“እቃቃ” ጨዋታን በዘመነ፣ ምቾቱና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ለትውልዱ ያቀረበ ድንቅ ማዕከል ነው።

ሕጻናት ወደዚህች ማዕከል ከገቡ በኋላ የራሳቸውን ውስጣዊ ፍላጎት መነሻ በማድረግ የሚፈልጉትን ሙያዊ ሚና ይመርጣሉ። እንደ ፍላጎታቸው የባንክ ሠራተኛ፣ የካፌ ባለሙያ ወይም ፖሊስ በመሆን ያንን ገጸ-ባህሪ በተግባር እየተጫወቱ እርስ በርሳቸው ማኅበራዊ ትስስር ይፈጥራሉ።

የማዕከሉ መስራችና ሥራ አስፈጻሚ አስናቀች ንጉሴ ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት ፣ የማዕከሉ ዋና ዓላማ ሕጻናት-መር የሆነ የመጫወቻ ማዕከል መሆን ነው።

በመሆኑም በከተማዋ ውስጥ የልጆችን ደህንነት ከመከታተል ውጪ “ይሄን አትንኩ ፣ ያን አታድርጉ” የሚል ምንም ዓይነት የነፃነት ገደብና ክልከላ እንደሌለ ወይዘሮ አስናቀች ተናግረዋል።ይህም ሕጻናት ሙሉ በሙሉ በነፃነት የራሳቸውን ዓለም መስርተው እንዲያለሙና በራሳቸው እንዲተማመኑ ያደርጋቸዋል።

ወላጆች በሥራ በሚጠመዱበትና ቤት ውስጥ ልጆችን የሚጠብቅላቸው ሰው በማያገኙበት ጊዜ ልጆቻቸውን እዚህ ማዕከል በአደራ አስረክበው የራሳቸውን ጉዳይ ማከናወን እንደሚችሉ ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።

የልጆች መዝናኛ ማዕከሉ ከማክሰኞ እስከ እሁድ በየቀኑ ከጠዋት ሦስት ተኩል እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ድረስ ክፍት ሆኖ አገልግሎት እንደሚሰጥ ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።

የአራዳዋ ትንሿ ከተማ ለሕጻናት ጊዜያዊ መጫወቻ ብቻ ሳትሆን ነገ ሐገር የሚረከቡበትን ማኅበራዊ ኃላፊነት በጨዋታና በነፃነት የሚለማመዱበት የሕይወት ትምህርት ቤት ሆና አገልገሎት እየሰጠች ትገኛለች።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review