AMN – ግንቦት 12/2018 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ በአደስ ከተማ ክፍለ ከተማ ገብስ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ቁጥር 3 የበጎነት መንደር የተገነባውን 44 የመኖሪያ ቤቶች እና ሱቆች ያሉት ባለ አምስት ወለል ህንጻ ለተጠቃሚዎች አስተላልፈናል ብለዋል፡፡

ገብስ ተራ ቀደም ብሎ እጅግ የተጎሳቆለ እና ለመኖር ምቹ ያልሆነና ባረጁ እና በደቀቁ ቤቶች የተሞላ፤ በተደጋጋሚ በእሳት አደጋ የሚጠቃ፣ ለአቅመ ደካማ እናቶች የማብሰያና የመጸዳጃ አገልግሎት አስቸጋሪ የነበረበት መንደር ነበር ብለዋል ከንቲባ አዳነች።
ከንቲባ አዳነች አክለውም በዚህ መንደር የዛሬውን ጨምሮ በአጠቃላይ 377 የመኖሪያ ቤቶች ያላቸው 5 ህንጻዎችን መገንባት የቻልን ሲሆን ነዋሪዎቻችንም ከዛ አስከፊ አኗኗር ተላቀው ክብራቸውን በሚመጥን ፅዱ፣ ዘመናዊ አኗኗር የሚፈጥር፣ ልጆች ቦርቀዉ የሚጫወቱበት እና ደረጃውን በጠበቀ መኖሪያ መንደር እንዲኖሩ በማድረጋችን በጣም ደስ ብሎናል ብለዋል።

በዚህ የበጎነት መንደር ግንባታ ላይ በክትትል እና ድጋፍ አስተዋጽኦ ያደረጉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮቻችን ከምንም በላይ ልበ ቀና ባለሀብቶች በገንዘባቸው ላደረጉት ድጋፍ በነዋሪዎቹ ስም ከልብ አመሰግናለሁ ብለዋል ከንቲባ አዳነች በመልዕክታቸው።