የዓለም የስፖርት መዲና የተሰኘችው ባኩ እና አዲስ አበባ

You are currently viewing የዓለም የስፖርት መዲና የተሰኘችው ባኩ እና አዲስ አበባ

AMN- ግንቦት 13/2018 ዓ.ም

የአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ የዓለም ስፖርት ዓይን እየሆነች መጥታለች። ውቧ ከተማ ከአውሮፓ አልፋ የዓለም ቀልብ እንድትገዛ ያደረጋት በቅርብ ዓመታት ለስፖርቱ የሰጠችው ትኩረት ነው።

የአዘርባጃን ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር ፋሪድ ጋዲቦቭ ከዩሮ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ በቅርብ ዓመታት በባኩ እና ዙሪያዋ ከ200 በላይ የስፖርት ማዕከላት እንደተገነቡ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ሀገራቸው ለስፖርቱ የሰጠችው ቦታ “የዓለም የስፖርት መዲና” እንዲሰኙ በር ከፋች መሆኑን ይገልጻሉ። በተለይ በተያዘው ዓመት 2026 የተለያዩ ዓለም አቀፍ የስፖርት ሁነቶች ወደ ባኩ መጉረፋቸው የሀላፊውን ንግግር አጉልቶ ያሳያል።

ባኩ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርቶች ማዕከላትን መያዟ ይበልጥ ተመራጭ አድርጓታል። በ2026 የፎርሙላ ዋን የአዘርባጃን ግራንድ ፕሪ ጨምሮ፣ የማርሻል አርት፣ ቦክስ፣ ቮሊቦል፣ እጅ ኳስ ፣ ውሃ ዋና እና ሌሎች ስፖርቶችን በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሃላፊነቱን ወስዳ አዘጋጅታለች፤ እያዘጋጀችም ትገኛለች።

የአዘርባጃ ፎርሙላ ዋን ግራንድ ፕሪ ከ2016 ጀምሮ በባኩ እየተከናወነ ይገኛል። ታላቁን የመኪና እሽቅድምድም ማዘጋጀቷ በረከቱን አዝንቦላታል። በዝግጅቷ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ብቻ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ እስከ 277 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ማግኘቷን የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል።

አዘርባጃን ባለፈው ዓመት ፎርሙላ ዋንን በማሰናዳቷ እስከ 13 ሺ ሰዎች መዳረሻቸው እንዳደረጓት “ካሊበር” የተሰኘው የሀገሪቱ የዜና ምንጭ ዘግቧል።

ስፖርት ከገቢ ምንጭነቱም ባለፈ ገጽታዋን የገነባላት ባኩ ከበርካታ የስፖርቱ አስተዳዳሪ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችላት ስምምነት እየፈጸመችም ትገኛለች። ስፖርታቸውን ለማሳደግ የሚደረጉ ሀሳብ የመስጫ መድረኮችም ባኩን መምረጥ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

አዘርባጃን ዓለም በጉጉት የሚጠብቃቸውን ስፖርታዊ ሁነቶችን ከማሰናዳት ባለፈ ጠንካራ ተሳትፎም ለማድረግ ስፖርተኞቿ በቂ ስልጠና እንዲያገኙ የሄደችበት ርቀት ትኩረት የሚስብ ነው።

ሁሉን አቀፍ ስልጠና በማዘጋጀት በርካታ የሀገሬውን ሰው በማሳተፏ ሙገሳ ተችሯታል። በተለይ በስፖርቱ የሴቶችን ተሳትፎ 40 በመቶ ማድረሷ አስመስግኗታል። ለውጡም በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ ስፖርተኞችን እንድታፈራ መንገድ ከፍቶላታል።

አዲስ አበባ የባኩን ለውጥ በደንብ ተገንዝባለች። በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የስፖርትን ሃይል የተረዳው መንግስት ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ውድድሮች በመዲናዋ እንዲከናወኑ አድርጓል።

የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ ጨምሮ ባሳለፍናቸው ጥቂት ወራት የተዘጋጁት ዓለም አቀፍ ውድድሮች አዲስ አበባ የባኩን መንገድ ለመከተል ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው።

ስፖርት የሚያስገኘው ገቢ እና የሚገነባው መልካም ገጽታ ባኩ እንዴት እንደተጠቀመችበት ለአዲስ አበባ መማሪያ መሆን ይችላል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review