የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ከማህበራዊ ፍትሕ እስከ ትውልድ ግንባታˮ
በቱም ቱም ሌንጮ

ረፋድ አምስት ሰዓት፤ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በአንዱ ክፍል ውስጥ የልጅ አንጀት የማይችለው ርሃብ፣ አዕምሮ ሊቀበለው የሚከብደው የመንፈስ ስብራት ነግሷል፡፡ ከክፍሉ በአንደኛው ጥግ ተማሪ ፈቃዱ የኔነህ የተማሪዎች ወንበር ላይ የተቀመጡ ደብተሮቹን ተደግፎ ተኝቷል። መምህሩ ጥያቄ ሲጠይቁ እጁን አውጥቶ የማይመልሰው፣ አይኖቹን ግን ግድግዳው ላይ የተሰቀለው ሰዓት ላይ የሚያንከራትተው ፈቃዱ፣ ሁል ጊዜ ጠዋት ትምህርት ቤት ሲመጣ በእጁ የላስቲክ ምሳ ዕቃ መያዝ አይረሳም።
ይሁን እንጂ የትምህርት ክፍለ ጊዜው መጠናቀቁንና የምሳ ሰዓት መድረሱን የሚያስታውሰው የደወል ድምፅ ሲሰማ ፈቃዱ ጓደኞቹ ዘወትር ምሳቸውን ወደሚመገቡበት ስፍራ አይሄድም። ይልቁንም የምሳ ሳህኑን እንደያዘ በግቢው ጥግ ወዳለችው ዛፍ ጥላ ስር ብቻውን ያመራል። ይህን ከሌሎች ተማሪዎች የተለየ የዘወትር ተግባር በተደጋጋሚ ይመለከቱ የነበሩት መምህሩ፣ ተማሪ ፈቃዱ ወዳረፈባት ዛፍ ስር አቀኑ፤ ብቻውን የተቀመጠውን አዳጊ ተጠግተው የምሳ ዕቃውን ሲከፍቱት ግን ውስጡ ምንም ምግብ አልነበረም፤ ባዶ ነበር! ፈቃዱ ጓደኞቹ “ምሳ ዕቃ አልያዝክም” ብለው እንዳያገልሉትና እንዳያፍር ብቻ ነበር ባዶ ምሳ ዕቃ ተሸክሞ ወደ ትምህርት ቤት የሚያቀናው። ከሰዓት በኋላ ባለው ክፍለ-ጊዜ፣ የርሃብና የድካም ስሜት የሚጠናበት ፈቃዱ በክፍል ውስጥ ተዝለፍልፎ መውደቅ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመው ክስተት ነበር።
ይህ ታሪክ የፈቃዱ ብቻ አልነበረም፤ የትምህርት ቤት ምገባ ከመጀመሩ በፊት በከተማችን ትምህርት ቤቶች ውስጥ የነበረው የችግር ጥልቀት ማሳያ እንጂ። ተማሪዎች ምግብ ባለመመገባቸው ምክንያት በክፍል ውስጥ ተዝለፍልፈው መውደቅ፣ ለትምህርታቸው ትኩረት ማጣት፣ በዚህም ሳቢያ የውጤት መቀነስ፣ መጠነ-መድገም፣ መጠነ-ማቋረጥና መጠነ-ማርፈድ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሄዱ የከተማ አስተዳደሩን አስገዳጅና አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ ያስገደደው መነሻ ነበር።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በከተማዋ ትምህርት ቤቶች መጀመር እንደ ፈቃዱ ያሉ አዳጊዎችን የየዕለት ጭንቀት አቅልሏል፤ የእናቶችን እምባ አብሷል፡፡ ይህ ተግባር ተማሪዎችን የመመገብ ተራ የበጎ አድራጎት ስራ አይደለም፤ ይህ የከተማዋን የትምህርት ጥራት የሚቀይር፣ ማህበራዊ ፍትሕን የሚያሰፍን እና የነገዋን ጠንካራ አገር የሚቀርጽ ግዙፍ የትውልድ ግንባታ ፕሮጀክት ነው።
የማህበራዊ ፍትህ ማረጋገጫ ድልድይ

ማህበራዊ ፍትሕ (Social Justice) ማለት ሁሉም ዜጋ እኩል የመደመጥ፣ የመማር እና የመልማት እድል ሲያገኝ ነው። በአንድ ክፍል ውስጥ ምሳ ይዞ የሚመጣ ተማሪ እና እንደ ፈቃዱ ባዶ ምሳ ዕቃ ይዞ የሚቀመጥ ተማሪ እያለ ስለ “እኩልነት” እና ስለ “ትምህርት ጥራት” ማውራት አይቻልም። ርሃብ ባለበት ክፍል ውስጥ ዴሞክራሲም ሆነ ፍትሕ ቦታ የላቸውም።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ክፍተት ለመድፈን የተማሪዎችን የምገባ ፕሮግራም እንደ ዋና የማህበራዊ ፍትሕ ማስፈኛ መሳሪያ አድርጎ ሰርቷል። መርሃ ግብሩ ሲጀምር 300 ሺህ ተማሪዎችን ብቻ ያቀፈ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ከ1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን በቀን 2 ጊዜ ጥራቱ የተጠበቀና ጤናማነቱ የተረጋገጠ ምግብ መመገብ ተችሏል፤ በተጨማሪም ዩኒፎርም፣ ጫማ እና የመማሪያ ቁሳቁስ ጭምር ለተማሪዎቹ ያቀርባል።
ይህን ያህል ቁጥር ያለውን ተማሪ በየቀኑ የተመጣጠነ ይዘት ያለው ቁርስና ምሳ መመገብ ማለት ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡ በቀላሉ ለመመልከት ይህ አሃዝ ከሲሼልስ የሕዝብ ብዛት ስምንት እጥፍ በላይ እንደማለት ነው፡፡ ይህ ማለት አዲስ አበባ የሲሼልስን ያህል ቁጥር ያላቸው ስምንት ሀገራትን በየቀኑ ቁርስና ምሳ ትመግባለች፤ በየዓመቱ የትምህርት ቤት ደንብ ልብስ፣ ጫማ፣ ደብተርና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁስ ታሟላለች እንደማለት ነው፡፡ በእርግጥ ጉዳዩን በጥልቀት ካየነው ከዚህም በላይ ትርጉም የሚሰጥ ነው፡፡
ይህ እርምጃ በከተማዋ ሰፊ ማህበራዊ ፍትሕን አስፍኗል፤ በኢኮኖሚ አቅም ማነስ ምክንያት ልጆቻቸውን መመገብ የማይችሉ ወላጆችን ትልቅ ሸክም አቅልሏል። ከ16 ሺህ በላይ አቅመ ደካማ መጋቢ እናቶችን በቅንጅት በማደራጀትና የስራ እድል በመፍጠር፣ የኢኮኖሚ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን አረጋግጧል፤ ቋሚ የስራ እድልም ፈጥሯል። አሁን በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሁሉም ተማሪዎች እኩል ይመገባሉ፣ እውቀት ይገበያሉ፤ እናም የነገ ተስፋቸውን በብሩህ ተስፋ አሻግረው ይመለከታሉ።
በትምህርት ቆይታ ላይ የመጣ ለውጥ

ይህ ማህበራዊ ፍትሕን የማስፈን ስራ ዝም ብሎ በበጎ ምኞት የተገለጸ ሳይሆን በተጨባጭ ቁጥሮች የተደገፈ ስኬት ያመጣ ነው። በተለይም ተማሪዎች በምግብ እጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡበት ሁኔታ ግርምትን በሚፈጥር መልኩ ቀንሷል፡፡
ይህ መሻሻል በተማሪዎች አጠቃላይ የክፍል ውስጥ ውጤት፣ በተለይም በ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናዎች የማለፍ ምጣኔ ላይ ተጨባጭና አስደናቂ ለውጥ እንዲመዘገብ አድርጓል።
“ሀገር የሚገነባው በዜጎች ሁለንተናዊ ለውጥና በትውልድ ግንባታ ቀጣይነት ነው!”
የፕሮግራሙ ትልቁ ስኬት እንደ ተራ ምጽዋት ሳይሆን እንደ ትልቅ “የትውልድ ግንባታ” ፕሮጀክት መታሰቡ ነው። ዛሬ በትምህርት ገበታ ላይ እያለ አእምሮው በዕውቀት፣ አካሉ ደግሞ በተመጣጣኝ ምግብ ያልተገነባ አዳጊ፣ ነገ አገር የመረከብ ተስፋው የመነመነ ነው።
ይህ ፕሮግራም ለወደፊቱ ብቁ፣ አገር ወዳድ፣ ጤናማ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችል ትውልድ ለመፍጠር ትልቁን ሚና ይጫወታል። ዛሬ በትምህርት ቤቶች እየተተገበረ ያለው የምገባ ፕሮግራም ነገ ለአገሪቱ የሳይንስ ሊቃውንትን፣ መሀንዲሶችን፣ መሪዎችን እና የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን የሚያፈራበት የትውልድ ማሳደጊያ ስልት ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን ፕሮግራም በዘላቂነት ለማስቀጠልና ስኬታማ ለማድረግ ልዩ የፖለቲካ ቁርጠኝነት አሳይቷል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ስራውን በዘመናዊ መዋቅር ተቋማዊ አድርጎ ለመምራት ራሱን የቻለ “የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ” ማቋቋሙ ነው። ከዚህም ባሻገር በጥራት ረገድ ጉድለት እንዳይኖር በሁሉም ትምህርት ቤት ሁለት ሁለት የስነ-ምግብ ባለሙያዎችን በመቅጠር ጠንካራ የክትትል ስርዓት ዘርግቷል።

ይህ የአዲስ አበባ ከተማ ተሞክሮ ዛሬ የሀገር ውስጥ ስኬት ብቻ አይደለም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ እውቅናን ያገኘ፣ ለኢትዮጵያ መልካም ገፅታ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ ያበረከተና ሌሎች አዳጊ አገሮችም ሊቀስሙት የሚገባ ትልቅ ሞዴል ሆኗል።
ዛሬ እንደ ፈቃዱ ያሉ የከተማችን ልጆች ምሳቃቸው ባዶ አይደለም፤ የቀደመ ታሪካቸውም ላይመለስ ትዝታ ሆኖ አልፏል፡፡ ባዶ ምሳ እቃ ይዞ በመመላለስ ምክንያት ይደርስባቸው የነበረው የመንፈስ ስብራት ተጠገኖ ልባቸው በፍቅር፣ በእኩልነት እና በተቃና የነገ ተስፋ ተሞልቷል።
በቱም ቱም ሌንጮ