AMN- ነሐሴ 15/2018 ዓ.ም

«ጽናት፡ የምስራቅ አፍሪካ የጤና ኢኮኖሚን መገንባት» በሚል መሪ ሀሳብ ከነሐሴ 15 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ 3 ቀናት በአዲስ አበባ አደዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ባለው በዚህ ጉባኤ፣ ከ20 ሀገራት የመጡ ከ2ሺ 600 በላይ መሪዎች፣ ባለሀብቶች፣ ተመራማሪዎች፣ ባለሙያዎች እና የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ከ585 ሚሊዮን በላይ ህዝብን የሚወክሉ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የጤና ዘርፍ ተወካዮች፣ የፖሊሲ አውጪዎችና የግል ባለሀብቶች በአንድ ጣሪያ ስር ተሰባስበዋል። ከውጭ የሚገቡ መድኃኒቶችንና የሕክምና መሣሪያዎችን ጥገኝነት ለመቀነስ፣ በቀጠናው ውስጥ ነፃ የንግድ ቀጠናን በመጠቀም ምርቶችን ለማሰራጨት እና የሕክምና ፋይናንስን ለማጠናከር ያለመ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
የጉባኤው ዋና ዓላማ ቀጠናዊ ትብብርን ለማጠናከር፣ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት፣ የሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓትና ምርትን ለማሳደግ እና የህክምና አገልግሎት ጥራትን ማረጋገጥ መሆኑ ተመላክቷል።
አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ጉባኤዎችና ትብብሮች እያደጉ መምጣታቸው የጤና ኢኮኖሚን ከማጠናከር ባለፈ አፍሪካ 99 በመቶ የሚሆነውን የክትባት እንዲሁም 70 በመቶ የሚሆነውን የመድኃኒት ፍላጎት በራሷ አቅም ለማሟላት ምቹ አጋጣሚ ይፈጥርላታል።
አፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ አቅሟን አሳድጋ የራሷን የሕክምና መድኃኒቶችና መሣሪያዎች በሀገር ውስጥ የማምረት ራዕይ ሰንቃለች። ዛሬ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የተከፈተው 13ኛው የምስራቅ አፍሪካ የጤና ፌዴሬሽኖች ጉባኤም ዋነኛ ትኩረቱ ይህንን ራዕይ ከግብ ለማድረስ መደላድሎችን መፍጠር ነው።
ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባኤ ላይ ከ100 በላይ የዘርፉ ልሂቃን ጥናታዊ ጽሑፎችንና የፓናል ውይይቶችን የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ጎን ለጎንም ከ80 በላይ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የፈጠራ ውጤቶቻቸውንና የሕክምና ቴክኖሎጂዎቻቸውን ያስተዋውቃሉ።
ኢትዮጵያ ይህን ታላቅ ቀጠናዊ ጉባኤ እንድታዘጋጅ ለመመረጥ ካደረጓት ዋነኛ ምክንያቶች መካከል ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጤናው ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ተጨባጭ ስኬቶች መሆናቸው ይጠቀሳሉ።
ሀገሪቱ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋፋት፣ የእናቶችና ሕፃናት ሞትን በመቀነስ፣ እንዲሁም የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾችን በማበረታታትና የዲጂታል ጤና ሥርዓትን በመዘርጋት ረገድ ያሳየችው እመርታ ለቀጠናው ሀገራት በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑ በጉባኤው ላይ ተመልክቷል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም የመዲናችን አዲስ አበባ አስተዳደር የሆስፒታሎችንና የጤና ጣቢያዎችን ቁጥር በእጅጉ በማሳደግ፣ ዘመናዊ የሕክምና ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ እና የጽኑ ህሙማን ህክምና አቅምን በማጎልበት ረገድ ያስመዘገበችው ስኬት ለቀጠናው ከተሞች በምሳሌነት የሚጠቀስ እንደሆነ ተገልጿል።
ለጤና ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአዳዲስ ዘመናዊ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ግንባታና እደሳት እንዲሁም በጤና ቱሪዝም ዘርፍ ተጨባጭ ለውጦችን ላስመዘገበችው መዲናችን አዲስ አበባም ይህን ቀጠናዊ ጉባኤ ማስተናገድ ልዩ ትርጉም አለው።
በይታያል አጥናፉ