የአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ ለኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

AMN ግንቦት 19 ቀን 2018

የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ለ1 ሺህ 447ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ ዓሊ ዩሱፍ በአፍሪካና በመላው ዓለም ለሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ለኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

ሊቀመንበሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ይህ የተቀደሰ በዓል የእምነት፣ የርህራሄ እና የአንድነት እሴቶች የሚንጸባረቁበት መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ ዕሴቶች አፍሪካ የላቀ ሰላም፣ አንድነትና ሰብአዊ ክብርን ለመገንባት ለምታከናውናቸው ተግባራት ዘላቂ መነሳሳትን እንደሚፈጥሩ አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም በዓሉ በአፍሪካ ሕዝቦች መካከል ያለውን የወንድማማችነት ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክርና በአህጉሪቱ ላይ የታደሰ ተስፋን፣ ብልጽግናን እንዲሁም ስምምነትን እንደሚያሰፍን ያላቸውን ጽኑ ምኞት ገልጸዋል።

በተያያዘም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ ለኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዋና ፀሐፊው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ በዓሉ መሥዋዕትነት፣ ቁርጠኝነትና ደግነት የሚንጸባረቅበት በመሆኑ፤ የእነዚህን መልካም እሴቶች መንፈስ በማሰብ ሊከበር እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዓሉ ከቤተሰብ እና ከጓደኞች ጋር የሚደረግን ደስታ ይበልጥ የሚያጎላና በበረከት የተሞላ ውብ ቀን እንዲሆንም መመኘታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review