የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የገበያ ማረጋጋት ስልቶች!

የመንግሥት ዋነኛ ተልዕኮ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻልና የኑሮ ደህንነትን ማረጋገጥ ነው። ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ የገጠማት የኑሮ ውድነት መነሻው ከለውጡ በፊት የነበረው ጤናማ ያልሆነ የፋይናንስ ሥርዓት መአንዱ ምክንያት ነው ። በወቅቱ የነበረው ልል የገንዘብ ፖሊሲ፣ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም፣ እንዲሁም ያልዘመነ የንግድ አሠራር ለከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መንስኤ ሆነው ቆይተዋል። ይህን ሥር የሰደደ ችግር ለመፍታት መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ መዋቅራዊ ለውጦችን በማድረግ ገበያውን ለማረጋጋት መጠነ ሰፊ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ውስጥ የተካተቱት የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠሪያ እርምጃዎች በአሁኑ ወቅት በተግባር ላይ እየዋሉ ይገኛሉ። ለዋጋ ግሽበት ዘላቂው መፍትሔ የአቅርቦት እጥረትን መቅረፍ ነው ብሎ ያምናል። በዚህም መሠረት በአምራች ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ፣ በተለይም በግብርናና በኢንዱስትሪው ዘርፍ አዳዲስ ውጥኖች ተቀርፀው ተግባራዊ ሆነዋል። ከነዚህም መካከል በበጋ ስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት እና በ’’ኢትዮጵያ ታምርት’’ ንቅናቄዎች አማካኝነት ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ ተሠርቷል። እነዚህ ጥረቶች በዋናነት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የገበያ ጫናን ለመቀነስ ያለሙ ናቸው።

የግብርና ምርት አቅርቦትን ለማሳደግ የተከናወኑት ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያሳዩ ይገኛሉ። በተለይም በምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ ይስተዋሉ የነበሩ የዋጋ ንረቶች ትርጉም ባለው መልኩ እንዲቀንሱ ተደርጓል። መንግሥት ቀደም ሲል የነበረውን ያለ ዐቅም ገንዘብ የማተምና ከባንክ በመበደር ወጪን የመሸፈን የተሳሳተ አሠራር እንዲቆም አድርጓል። ይህ የፋይናንስ ሥርዓት ጥንቃቄ የገንዘብን የመግዛት ዐቅም ለማጠናከርና የዋጋ ንረትን ለመግታት ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

ከመደበኛ የኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነቶች በተጨማሪ፣ መንግሥት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ሲያስተባብር ቆይቷል። የበጎ ፍቃድ ድጋፎችን እና የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሮችን በማቀናጀት፣ ዜጎች እርስ በእርሳቸው እንዲደጋገፉ በማድረግ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ጫናውን እንዲቋቋሙ ተደርጓል። ይህ ማኅበራዊ ትስስር በኢኮኖሚ ቀውስ ወቅት የሕዝብን የመረዳዳት ባሕል በማሳደግ በኩል ከፍተኛ ፋይዳ ነበረው።

ባለፉት ወራት የተመዘገቡት የስታቲስቲክስ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ሀገራዊ የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ ረገድ ስኬቶች ተመዝግበዋል። በ2014 በጀት ዓመት 33 በመቶ የነበረው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት፣ በ2018 ተመሳሳይ ወር ወደ 10.9 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል። በተመሳሳይ ሁኔታ ምግብ ነክ የዋጋ ንረት ከ38.9 በመቶ ወደ 10.6 በመቶ ወርዷል። ይህም መንግሥት የጀመራቸው የሪፎርም ሥራዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን ያሳያል።

በቀጣዮቹ ዓመታት የዋጋ ንረትን ወደ ነጠላ አሃዝ ዝቅ ለማድረግ ግብ ተጥሎ እየተሠራ ይገኛል። ይህንንም ለማሳካት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጽዕኖውን የሚቀንሱ እርምጃዎችን ከመውሰድ ባሻገር፣ የዋጋ ግሽበትን ከመሠረቱ የሚፈቱ የረዥም ጊዜ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጦች ላይ በትኩረት መሥራቱን ይቀጥላል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review