AMN- ግንቦት 20/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሀገራዊ ምክክር ረቂቅ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ ተባባሪ አካላት ለሆኑ ሲቪክ ተቋማትና ማህበራት አቅርቦ ግብዓት አሰባስቧል፡፡
ዛሬ በተካሄደው መድረክ መልዕክት ያስተላለፉት ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕ/ር) ሲቪክ ተቋማትና ማህበራት በምክክሩ ሂደት ወሳኝ ሚና እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከተቋማቱ ጋር መሥራቱ የገለልተኛነት እሴትን ለማስጠበቅ አስችሎታልም ብለዋል፡፡
የውይይት መድረኩ የተዘጋጀው የምክክር ጉባኤው ከመከናወኑ በፊት ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ረቂቅ አጀንዳዎችን አሳውቀን ምክረሀሳብ ለማሰባሰብ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ ለሲቪከ ማኅበራትና ተቋማቱ የእስከ አሁኑ የአብሮነት ጉዞ ምስጋና በማቅረብ፤ የኮሚሽኑን የአራት ዓመታት ሂደት የሚያስቃኝ ገለጻም አድርገዋል፡፡

ሲቪክ ማኅበራትና ተቋማት በቀጣይ ለሚከናወነው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የጀመሩትን ጉልህ ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የተቀረጹ ረቂቅ የአጀንዳ ሀሳቦችን አስመልከቶ ገለጻ ያደረጉት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ፣ አጀንዳዎቹ በመጀመሪያ ደረጃ የረቂቅ ሂደት ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
የሚመለከታቸው አካላት ግብአት በስፋት ተካትቶበት እንደሚዳብርም ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አረጋግጠዋል፡፡

ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው፣ የሚቀረጹት አጀንዳዎች በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 6 መሠረት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በአዋጁ መሠረትም አጀንዳ የሚቀረጽበት መስፈርት ለሀገራዊ መግባባትና ሰላም የሚረዱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚታዩት ሀገርን ሊያስቀጥሉ የሚችሉ ሀገራዊ አጀንዳዎች መሆናቸውን የገለጹት ኮሚሽነር መላኩ፣ ሲቪክ ማኅበራትና ተቋማት ለሀገራዊ ጉባኤው ስኬት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ዕድሮች ጥምረት፣ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን፣ ኢትዮጵያንስ ፎር ኢንክሉሲቭ ዲያሎግ፣ ትምራን እና ዴስቲኒ ኢትዮጵያ መሳተፋቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡