የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ከምርጫ ቦርድና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ

AMN ግንቦት 21/2018

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሚካሄደውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ፣ በዶ/ር እስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ የተመራው የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ከምርጫ አስፈጻሚዎች እና ከሲቪል ማህበረሰብ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

በዉይይት መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት መሪዎችና ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ዶ/ር እስፔሲዮዛ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ጋር በምርጫ ዝግጅት፣ በምርጫው ዕለት የፀጥታ ሁኔታ፣ የቅሬታ መፍቻ መንገዶች እንዲሁም በድምፅ አሰጣጥ እና በውጤት አገላለጽ ሂደት ላይ ዉይይት አካሂደዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ቦርዱ የመራጮች እና የዕጩዎች ምዝገባን ያከናወነበትን “ምርጫዬ” የተሰኘውን የዲጂታል መተግበሪያ አስመልክቶ ማብራሪያ ተሰጥቷል። የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እና በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችም በዚሁ የውይይት ወቅት ተብራርተዋል።

የታዛቢዎች ቡድኑ ከኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ጋር ያደረገው ውይይት ሴቶች በመልካም አስተዳደር እና በፖለቲካ ሂደት ውስጥ ባላቸው ሚና ላይ ትኩረት ያደረገ ነዉ፡፡

በዚህም ፌዴሬሽኑ በሰላም ግንባታ እና በብሔራዊ ምክክር ሂደት ላይ እያደረገ ያለውን ጥረት የገለጸ ሲሆን፣ በመላው ኢትዮጵያ የሰለጠኑ ከ10 ሺህ በላይ ሴት ታዛቢዎችን ማሰማራቱን ለታዛቢ ቡድኑ አስታውቋል።

ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት ጋር በነበረው ቆይታም፣ ስለቅድመ ዝግጅት፣ ስለታዛቢዎች ስምሪት እንዲሁም የምርጫው ሂደት ሰላማዊ፣ ተአማኒ ፣ ግልጽ እና አካታች እንዲሆን በባለድርሻ አካላት መካከል ጠንካራ ትብብር መፍጠር አስፈላጊ ስለመሆኑ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

እነዚህ ውይይቶች በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ እና ተአማኒነት ያለዉ የምርጫ ሂደት እንዲኖር ለመደገፍ ኢጋድ ከባለድርሻ አካላት ጋር እያደረገ ያለው ሰፊ ግንኙነት አካል መሆኑ ተገልጿል።

በወንድማገኝ አሰፋ

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review