AMN-ግንቦት 20/2018 ዓ.ም

አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ በሚገኝ የኢራን ድሮን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ፤ ኢራን በአጸፋዉ የአሜሪካንን የአየር ኃይል የጦር ሰፈር ኢላማ ያደረገ ጥቃት ፈጽማለች፡፡
ይህ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ግጭት፤ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ጦርነትን ለማስቆም እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ሲደረግ የነበረዉን ድርድር ማስተጓጎሉ ተገልጿል፡፡
አሜሪካ ጥቃቶቹን የወሰደችዉ ወታደሮቿን ከጥቃት ለመከላከል መሆኑን የገለጸች ሲሆን፣ አሜሪካ በሶስት ቀናት ውስጥ በኢራን ውስጥ የሚገኙ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ስትሰነዝር ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባቃኢ የአሜሪካንን ጥቃት ያወገዙ ሲሆን፣ ጥቃቶቹ የተኩስ አቁም ስምምነቱን የጣሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ እንደተናገሩት ከሆነ አሜሪካ ከድርጊቷ የማትቆጠብ ከሆነ ኢራን የሀገሯን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ ትወስዳለች፡፡
ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአሜሪካ ጦር ሰፈር የምታስተናግደው ኩዌት በበኩሏ፣ ጥቃቶቹ ከየት አቅጣጫ እንደተሰነዘሩ ባትገልጽም ለሚሳኤል እና ድሮን ጥቃቶች ምላሽ እየሰጠች መሆኑን አስታውቃለች።
በሌላ በኩል እስራኤል፤ በሊባኖስ ላይ የምትወስደዉን እርምጃ አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን በኢራን ድጋፍ ይደረግለታል ያለችዉን የሂዝቦላ መሠረተ ልማቶችን መምታትዋን ገልጻለች፡፡
በመካከለኛዉ ምስራቅ አዲስ የተቀሰቀሰዉን ግጭት ተከትሎ የአሜሪካ ድፍድፍ ነዳጅ፤ ቅናሽ አሳይቶ ከነበረበት ከፍ ማለቱ ተዘግቧል:: የአክሲዮን ገበያዎች ዋጋ ሲያሽቆለቁል፣ የአሜሪካ ዶላር ደግሞ ጭማሪ አሳይቷል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በሃገራቸዉና በኢራን መካከል እየተደረገ ያለዉን ድርድር አስመልክቶ ለካቢኒያቸዉ ሰሞኑን ባደረጉት ንግግር መቼም ቢሆን ኢራን የኑክሌር መሣሪያ አይኖራትም ሲሉ አቋማቸውን ማንጸባረቃቸዉን ቢቢሲና ሮይተርስ ዘግበዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ