የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ እመርታ በአፍሪካ ሰማይ ስር!

AMN ግንቦት 21/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫዋ ዋዜማ፣ ዜጎች በሰከነ መንፈስ ውሳኔያቸውን በሚያመዛዝኑበት የታሪካዊ የጥሞና ጊዜ ላይ ትገኛለች።

ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን ለመራጭነት በነቂስ በማሳተፍም፣ በአፍሪካ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስና ደማቅ ምዕራፍ እየጻፈች ነው።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲሁም ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መጎልበት መሠረት የጣሉ ተግባራት፣ የነፃ እና ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ በፅኑ መሠረት ላይ መቆም፣ የዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ በነጻነት መንፈስ መስፋት እና የተፎካካሪ ፓርቲዎች በነቃ ተሳትፎ መውጣት ለዚህ ታላቅ ሂደት ስኬት ዋነኛ ምሰሶዎች ሆነዋል።

ከዚህ በተጨማሪም፣ የዜጎች ከወትሮው የተለየ በሀገር ጉዳይ ላይ የባለቤትነት ስሜት መዳበር፣ የፖለቲካ ተሳትፎ እና ተነሳሽነት መጨመር፣ የምሁራን ስልጡን የፖለቲካ ትንተና እና አማራጭ የ”ቢሆን” መፍትሄዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እውቀትና ሃሳብን መሠረት አድርገው ያካሄዷቸው የምርጫ ክርክሮች፣ ፍጹም ሰላማዊና ስልጡን የነበረው የምረጡኝ ቅስቀሳ እንዲሁም የሚዲያው ሚዛናዊና ንቁ ሚና ለዚህ ታላቅ ሀገራዊ ክንውን ተጨማሪ ድምቀት ሆነዋል።

መራጩ ህዝብ በቁጥር ደረጃ ሲታይ፣ በአህጉሪቱ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ካላቸው ጥቂት ሀገራት ተርታ የሚሰለፍ መሆኑ፣ ሀገሪቱ የጀመረችውን የዲሞክራሲ ሥርዓት የማጽናትና ተቋማትን የመገንባት ታሪካዊ ጉዞ በእጅጉ ያፋጥነዋል።

ይህ ታሪካዊ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ብሎም መላው አፍሪካ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ተገዥና ተመልካች ብቻ ሳይሆኑ፣ የራሳቸውን እጣ ፈንታ በራሳቸው መወሰን የሚችሉ ግንባር ቀደም ተዋናዮች መሆናቸውን ለመላው ዓለም በተግባር ያረጋገጡበት ደማቅ አጋጣሚ ሆኖ በታሪክ መዝገብ ላይ ይሰፈራል።

ይህ ታላቅ ህዝባዊ ንቅናቄ፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሥልጣን ምንጭ በጦር አፈሙዝ ስሌት ወይም በሴራ ሳይሆን፣ በዜጎች ንቁ ተሳትፎና በሚስጥር በሚሰጥ የምርጫ ካርድ ብቻ የሚወሰን መሆኑን በፅኑ ያበስራል። የመራጩ ቁጥር በ2013 ዓ.ም ከነበረበት 38.2 ሚሊዮን አሁን ወደ 54+ ሚሊዮን ማሻቀቡ፣ ለሰለጠነና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አስተማማኝ መሠረት የሚጥል ታሪካዊ እመርታ ከመሆኑም በላይ፣ ለነገዋ የበለጸገችና የተረጋጋች ኢትዮጵያ የማይናወጥ የሰላም ዋስትና ነው።

በቱም ቱም ሌንጮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review