ተቀጥራ ከምትሰራበት መኖሪያ ቤት ከ1ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ ንብረቶችን የሰረቀች ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለች

AMN- ግንቦት 21/2018 ዓ.ም

ተከሳሽ ዓለም ሲሳይ የተባለች የስርቆት ወንጀሉን የፈፀመችው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በልዩ ስሙ አትሌቶች መንደር ነው።

ተጠርጣሪዋ በግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት ያለ ምንም ተያዥ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ የአሰሪዎቿን እንቅስቃሴ በሚገባ ስታጠና ትቆያለች።

በተቀጠረች በ9ኛ ቀኗ የተለያዩ አልባሳት እና መዋቢያ ጌጣጌጦችን፣ የአሜሪካን ዶላር 500፣ የቻይና ሀገር ዩዋን 400፣ የህንድ ሩፒ 600 የCCtv ካሜራ ዳይመንድ የጣት ቀለበት በአጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው ከ1.4 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ ንብረቶችን ሰርቃ ከአካባቢው ትሰወራለች።

የግል ተበዳይም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ ጎሮ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ቀርበው ተጠርጣሪዋ መሰወሯን ያመለክታሉ።

የጎሮ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ክፍል የደረሰውን መረጃ መነሻ በማድረግ ባደረገው ክትትል ተከሳሿን ከነሙሉ ኤግዚቢቱ ጋር በቁጥጥር ስር ያዉላታል።

በተጨማሪም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጥቷት የተወሰኑ ኤግዚቢቶችን በመሸሸግ የተባበራት ተጠርጣሪም ከሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3B-95611 አ/አ ጋር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዉሏል።

የከተማዉ ፖሊስ የምርመራ መዝገብ አደራጅቶ ለክፍሉ አቃቤ ህግ በማቅረብ ክስ እንዲመሰረትባቸው አድርጓል።ድ

ህብረተሰቡ ማንኛውንም ዓይነት ቅጥር ሲፈፅም ህጋዊነትን በተከተለ መልኩ ቢሆን የተሻለ መሆኑን ያስገነዘበው የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አካላትም ከወንጀል ፈፃሚዎች ጋር በጥቅም ተሳስረው የወንጀል ተጠያቂ ላለመሆን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አሳስቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review