AMN – ግንቦት 25 /2018 ዓ/ም
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት በሠላም መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የምርጫ ኮማንድ ፖስት አስታውቋል።
የድምፅ መስጫ ሂደቱ እስከ ከሌሊቱ 7፡00 ሰዓት ሲከናወን መቆየቱን በመጥቀስ ፣ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ የመስጠት ሂደት ፍጹም ሠላማዊ ሆኖ መጠናቀቁን የምርጫ ኮማንድ ፖስቱ ገልጿል።

በትራፊክ አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ግንቦት 24 ቀንም ሆነ ሌሊት ምንም አይነት ወንጀል አለመፈጸሙ ተገልጿል።
ድምጽ የመስጠት ስርዓቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ መራጩ ህዝብ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ዕጩዎች እና ታዛቢዎች ላበረከቱት አስተዋጽኦ እና ኃላፊነታቸውን በተገቢው ለተወጡ መላው የጸጥታ አካላት ኮማንድ ፖስቱ ምስጋናውን አቅርቧል።

ድምጽ ቆጠራው መቀጠሉን የገለጸው ኮማንድ ፖስቱ ፣ ድህረ ምርጫ ያለው ሂደት በተመሳሳይ በስኬት እንዲከናወን ባለ ድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተደራጀው የምርጫ ኮማንድ ፖስት ጥሪውን አቅርቧል።