ድምፅ የመስጠት ሂደቱ እና ቆጠራው በስኬትና በሰላም ተጠናቋል – የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ

You are currently viewing ድምፅ የመስጠት ሂደቱ እና ቆጠራው በስኬትና በሰላም ተጠናቋል – የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ

AMN – ግንቦት 26/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጄነራል አስራት ደኔሮ ድምፅ የመስጠት ሂደቱ እና ቆጠራው በስኬትና በሰላም መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

ጄነራል አስራት ሕዝቡ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች እና የጸጥታ አካላት የዚህ ስኬት ባለቤቶች በመሆናቸው ስኬታችንን ማጽናት ይጠበቅብናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የጸጥታ አካሉ ወገንተኝነት ለሕገ-መንግሥቱና ሕገ-መንግሥቱን መሠረት አድርገው ለሚወጡ ሕጎች ብቻ ነው።

በሕገ-መንግሥታችን ላይ የስልጣን ባለቤት ሕዝብ እንደሆነ እና የመንግሥት ስልጣን መያዝ የሚቻለው በምርጫ ብቻ መሆኑ ተደንግጓል።

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሕዝቡ በነቂስ በመውጣት መሪዎቹን ሲመርጥ ውሎ አምሽቷል።

ምርጫው ሕግን መሠረት በማድረግ እንዲፈጸም መላው የጸጥታ አካላት ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ ርብርብ በማድረጋቸው እና የሕዝቡ ድጋፍ ታክሎበት፣ ቅድመ ምርጫውንና የምርጫ ዕለቱን በስኬት ማጠናቀቅ ተችሏል።

በአሁኑ ወቅትም የድኅረ ምርጫው ሂደት በሰላም እየተከናወነ ይገኛል። ምርጫው በተያዘለት መርሃ-ግብር መሠረት እንዲከናወን ነዋሪው ያደረገው የነቃ ተሳትፎ፣ በተለይም በድምፅ መስጫው ዕለት ያሳየው ትዕግሥት የሚደነቅና ምስጋና የሚቸረው ተግባር ነው።

መላው የጸጥታ አካላት አመራሮችና አባላት፤ ደከመን ሰለቸን ሳትሉ የተጣለባችሁን ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነት በብቃት በመወጣታችሁ ኮርተንባችኋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ሁልጊዜ ለሥራችን ስኬታማነት ከጎናችን በመቆም እያደረጋችሁት ላለው ቀና ትብብር በዋና ጠቅላይ መምሪያው ስም ምስጋናዬን ሳቀርብ ታላቅ ክብር ይሰማኛል።

ምርጫውን ለማደናቀፍ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልሸረቡት ሴራ፣ ያልወጡት ዳገትና ያልወረዱት ቁልቁለት አልነበረም።

ሆኖም ግን ሴራቸው በሕዝብና በጸጥታ አካላት የጋራ ጥምረት ሳይሳካ ቀርቷል። ኢትዮጵያም መርጣለች፣ ከተማችን አዲስ አበባም መርጣለች።

የመንግሥት ስልጣን መያዝ የሚቻለው በምርጫ ብቻ መሆኑን ሕዝቡ ድምፁን በመስጠት መልዕክቱን አስተላልፏል።

በመሆኑም የስልጣን ባለቤት የሆነውን የሕዝብ ድምፅ ማክበር ከሁሉም ይጠበቃል።

አሁን ላይ የምርጫው ሦስተኛው ምዕራፍ ቀጥሏል፤ ውጤት ተገልጾ መንግሥት እስኪመሠረት ያለው ሂደት በተመሳሳይ መልኩ ስኬታማ እንዲሆን የሕዝቡ የነቃ ተሳትፎ እና የጸጥታ ተቋማት የወትሮ ዝግጁነት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ሀገርን የማጽናት ተግባር የጋራ ርብርብን ይጠይቃል፤ በሀገራዊ ምርጫው የተረጋገጠውም ይኸው ነው።

የጠላትን ሴራ በማክሸፍ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ እንዲሳካ ተልዕኳችሁን በብቃት የተወጣችሁ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሀገር መከላከያ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር፣ የከተማችን ደንብ ማስከበር፣ የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር፣ የሰላም ሠራዊት አመራሮችና አባላት የምርጫውን ደህንነት የማረጋገጥ ዓላማችሁ ተሳክቷል።

ሌት ተቀን የደከማችሁበት እንዲሁም የለፋችሁበት ተግባር በስኬት ተጠናቋል። ለፈጸማችሁት አኩሪ ተግባርም በምርጫ ኮማንድ ፖስቱ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ ማለታቸውን የመምሪያው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review