AMN – ግንቦት 26/2018 ዓ.ም
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ያከናወናቸው ተግባረታት የመዲናዋ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ እንዲሆን እንዳስቻለው የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ጥላሁን ካሳ ገለፁ፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጥራት፣ ፍጥነትና ብዝኃነትን በማቀናጀት ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን የሚያደርገውን ጉዞ ለማጠናከር ከኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለዉን የሥራ ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱንም የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ምክትል ስራ አስፈፃሚ እና የቴሌቪዥን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ካሳ እና የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ሌንሴ ገለታ ፈርመውታል፡፡
በዚሁ ወቅት የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ምክትል ስራ አስፈፃሚና የቴሌቪዥን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ካሳ፤ አጋርነቱ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር እያከናወናቸው ያሉ የበርካታ ስራዎች አንዱ አካል ነው ብለዋል፡፡
ተቋሙ መዲናዋን የሚመጥን በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ የዳበረ አሠራር እንደዘረጋ በማንሳት ይህ ስምምነትም ለሚተገብራቸው ሥራዎች ትልቅ አጋዥ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በተለያዩ ቋንቋዎች ይዘቶችን በልዩ ልዩ አማራጮች ወደ አድማጭና ተመልካች እያደረሰ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ጥላሁን ካሳ፤ ይህ ተግባርና ጥረት ተቋሙ የመዲናዋ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል።
ኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ የሰዎችን ሀሳብ የስራ ፈጠራና ጥረት በመደገፍ በሃገሪቱ የፋይናስ ስርዓት ውስጥ ጉልህ አስተዋፆ ያለው ጠንካራ የፍይናስ ተቋም ነው ብለዋል፡፡
ይህ ስምምነት ሚዲያው ከቀዳሚ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረው ብለዋል
የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ሌንሴ ገለታ በበኩላቸው፤ ባንኩ ከዘመኑ ጋር በፍጥነት እየተጓዘ የሚገኝ ቀዳሚ የፋይናስ ተቋም መሆኑን አስተዋል፡፡
ስምምነቱ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን የዳበረ ቴክኖሎጂ፣ ተደራሽነትንና አዳዲስ ፈጠራን በመጠቀም የፋይናንስ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ይበልጥ ለማስተዋወቅና ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
በራሄል አበበ