AMN ግንቦት 26/2018
የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የውጭ ግንኙነት መምሪያ ሊቀ መንበር ብፁዕ አቡነ አንቶኒ የተመራውን ልዑካን ቡድን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
የቮሎኮላምስክ ሜትሮፖሊታን እና የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሞስኮ ፓትርያርክ የውጭ ግንኙነት መምሪያ ሊቀ መንበር ብፁዕ አቡነ አንቶኒ ውይይቱን አስመልክተው እንደገለጹት፣ ከፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ጋር የተሳካ ውይይት አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በተደጋጋሚ የተጠቀሰች ታሪካዊ ሀገር መሆኗን አስታውሰው፤ አሁን ላይ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው ጥልቅ ደስታና ክብር እንደተሰማቸውም ገልጸዋል።
በሩሲያ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ግንኙነት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ መሆኑን አስታውሰዋል።

በሩሲያ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ግንኙነት በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናትም ሆነ በሀገሮቹ መካከል ለሚኖረው ታላቅ የወደፊት ተስፋ ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ያካሄደችው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ እና የተረጋጋ በሆነ መንገድ በመጠናቀቁም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እና የደቡብ ኦሞ እና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በበኩላቸው፤ ከፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ጋር የተደረገው የሁለቱን ሀገሮች ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ታሪካዊ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመው ውይይት እጅግ ፍሬያማና ስኬታማ እንደነበር ገልጸዋል።
የዚህ ዓይነቱ ግንኙነት በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን ወዳጅነት ይበልጥ ከማሳደጉም ባለፈ፣በሕዝብ ለሕዝብ እና በልማት ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት የጎላ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል።
በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ የሩሲያ ፌዴሬሽን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኤቭጌኒ ተሬኪን፣ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት መምሪያ የክርስቲያናዊ ግንኙነት ጉዳዮች ጸሐፊ ሂሮሞንክ ስቴፋን እንዲሁም የብፁዕ አቡነ አንቶኒ የግል ረዳት ቄስ አሌክሳንደር ኤርሾቭ መገኘታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡