AMN – ግንቦት 27/2018 ዓ.ም

ከ54 ሚሊየን በላይ ዜጎች የተመዘገቡበት ታሪካዊው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ ተጠናቋል።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለኤ ኤም ኤን በሰጡት አስተያየት፣ ከማለዳ ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ሳይሰለቹ በምርጫ ጣቢያዎች የተሰለፉት ዜጎች፣ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መፃፋቸውን ገልጸዋል።

የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብዱልቃድር አደም፣ ሀገርና መንግስት ሊመሰረት የሚገባው በምርጫ ብቻ መሆኑን እና በዜጎች ፍላጎትና ስምምነት ላይ የተመሰረተ መንግስት መመስረት እንዳለበት በፅኑ እንደሚያም ተናግረዋል።
በትጥቅ የፖለቲካ ፍላጎትን በኃይል ለማሳካት የሚደረጉ ሂደቶች ሀገራችንን ወደኋላ የሚጎትቱ በመሆናቸው፣ ስልጣን በምርጫ ብቻ የሚገኝበትን ስርዓት እንገነባለን ብለዋል።

የኢድሀን ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን ዓለምነው፣ በምርጫ ጣቢያዎች የታየው ረጅም ሰልፍ ዜጎች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነታቸውን በተግባር ያረጋገጡበት ታላቅ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
የአብን ተወካይ አቶ ማሩ ጃኔ ፣ ይህን እውን ለማድረግ ለ9 እና ለ10 ሰዓታት በሰልፍ የቆመው ህዝብ ሊመሰገን እና ሊከበር ይገባዋል ብለዋል።
የህብር ኢትዮጵያ ፓርቲ አቶ አበራ በቀለ እንደገለጹት፣ ይህ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ የስልጣን ሽግግር ማድረግ እንደሚቻል ያሳየ ትልቅ ማረጋገጫ ነው።

የኢዜማ መሪ አቶ እዮብ መስፍን በበኩላቸው፣ የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን ሂደቱ ትክክልና ፍትሃዊ እስከሆነ ድረስ ውጤቱን ለመቀበል ዝግጁ ነን በማለት ገልጸዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም የነበሩ ምርጫዎች ለይስሙላ እና ሁሉንም ያላካተቱ ነበሩ።

በዚህኛው ምርጫ ግን በሚዲያ አጠቃቀም ረገድ ለተፎካካሪዎች እኩል ዕድልና የሰዓት ክፍፍል የተደረገበት፣ የሃሳብ ብዝሃነት የሰፈነበት እና ሁሉም ፓርቲዎች በነጻነት የተሳተፉበት ፍትሀዊ መድረክ ነበር ብለዋል።
ህዝባችን ያሳየው ዲሞክራሲያዊ ጨዋነት ለሀገሪቱ የነገ ጉዞ በፅኑ መሰረት ላይ የጣለ ታላቅ ክስተት ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ