AMN – ግንቦት 28/2018 ዓ.ም

ንጹህና ምቹ አካባቢ ለሰዉ ልጆች ጤና፤ ደህንነት እና አጠቃላይ የኑሮ ሁኔታ ያለዉ ጠቀሜታ የላቀ ነዉ፡፡
ንጽህናዉ የተጠበቀ አካባቢ በቆሻሻ ውሃ ወይም በምግብ ብክለት አማካኝነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል ያግዛል፡፡
ንጽህናዉ የተጠበቀ አካባቢ በሰዉ ልጆች የአእምሮ እና የስነ-ልቦና ጤንነት ላይ ያለዉ ድርሻም የጎላ ነዉ፡፡ ንጹህ አየር፣ ንጹህ ውሃ እና ውብ መልክዓ ምድር የሰውን ልጅ የመንፈስ እርካታን ይጨምራል።

ንጽህናዉን ያልጠበቀ አካባቢ በመተንፈሻ አካላት ጤና ላይ የተለያዩ እክሎችን የሚፈጥር ሲሆን በአየር ላይ የሚሰራጩ ብናኞች፣ ከተቃጠሉ ቆሻሻዎች የሚወጣዉ ጭስ እና መጥፎ ጠረን ለጤና ጠንቅ ነዉ።
ንጹህናዉን የተጠበቀ አካባቢ ግን የአየር ጥራትን የሚያሻሽል ስለሆነ እንደ አስም፣ የሳንባ ኢንፌክሽን እና በሌሎች የመተንፈሻ አካል በሽታዎች የመያዝ እድልን በእጅጉ ይቀንሳል።
የአካባቢ ንጽህና ለሃገርም ሆነ ለግለሰብ ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። በሽታዎችን በመከላከል፣ ለህክምና የሚወጣውን የግለሰብ እና የመንግስት ወጪ ለመቆጠብ ያግዛል፡፡

ንጹህ እና ውብ ከተሞች ለቱሪስቶች ማራኪ በመሆናቸው ገቢን ይጨምራሉ፤ ለኢንቨስትመንትም ምቹ ናቸው።
የአካባቢ ንጽህና መጠበቅ የውሃ አካላትን፣ አፈርን እና አየርን ከመርዛማ ኬሚካሎች እና ከፕላስቲክ ብክለት ይከላከላል። ይህም ተፈጥሮ ራሷን እንድታድስ እና ለወደፊት ትውልድ ንጹህ ሀብት ለማስተላለፍ ያስችላል፡፡
የአካባቢ ንጽህና የአንድ ግለሰብ ወይም የመንግስት ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን የመላዉ ህዝብ የጋራ ኃላፊነት ነው።
እያንዳንዱ ግለሰብ ቆሻሻን በአግባቡ በመጣል፣ ዛፎችን በመትከል እና አካባቢውን በመንከባከብ ለጤናማ ማህበረሰብ ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላል።

በመዲናችን አዲስ አበባ የአካባቢ ጤናን ከመጠበቅ ረገድ በርከታ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን ከአሁን ቀደም ዋንኛ የጤና ጠንቅ የነበሩ ወንዞች ታክመዉና ጸድተዉ ወደ መዝናኛ ስፍራዎች ተቀይረዋል፡፡
በቆሻሻ ተዉጠዉ የነበሩ አካባቢዎችና ጎዳናዎች ዛሬ ላይ ጸድተዉ የእግረኛና የሳይክል መንገድ፤ የህዝብ መዝናኛ ፤ የስፖርት ማዘዉተሪያ፤ የህጻናት መጫወቻና የአይን ማረፊያ ሆነዋል፡፡
በከተማ ዉበትና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመንገድ ዳር፤ በወንዝ ዳርቻና በኮሪደር ልማት የተተከሉ ችግኞች ለአዲስ አበባ አዲስ ገጽታን ብቻ ሳይሆን አዲስ አየርና አዲስ ጠረንን ፈጥረዋል፡፡
የአካባቢን ጤናን ለመጠበቅ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የተሰሩት እነዚህ የልማት ስራዎች ተላላፊ በሽታዎችን ከመከላከልና የህብረተሰቡን ጤና ከማረጋገጥ ባሻገር አዲስ አበባን ለኑሮ ምቹና ለቱሪስቶችም ማራኪ እንድትሆን አድርገዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ