AMN ግንቦት 28 ቀን 2018 ዓ/ም
በረከት አረጋ የተባለ ግለሰብ የስርቆት ወንጀሉን የፈፀመው በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው ጉስቋም ቅድስት ማርያም አካባቢ ከምሽቱ 4:00 ሠዓት ላይ ነው።
ተጠርጣሪው በሠዓቱ ለኮሪደር ልማት ተዘርግቶ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብል በመጋዝ ቆርጦ በመውሰድ በውሃ ፍሳሽ መውረጃ ቱቦ ውስጥ ገብቶ ለመሰወር ይሞክራል።
በወቅቱ ስራ የነበሩ የፖሊስ አባላት ተከትለው በመግባት ሁለት ሰአት በፈጀ ፍለጋ ከነ ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር አዉለዉት አስፈላጊው ምርመራ እየተጣራበት መሆኑን የጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ ገልጿል ።

ወንጀል ፈፃሚው በወቅቱ ከነ ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር እንዲውል ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመሆን አስፈላጊውን ትብብር ማድረጉ የሚያስመሰግን ተግባር ነው ያለው ፖሊስ ህዝብ ሲተባበር ወንጀል ፈጻሚዎችን በቀላሉ ለህግ ማቅረብ እንደሚቻልም አመላክቷል።
የክፍለ ከተማው ፖሊስ ዋና መምሪያም ከአስተዳደሩ ጋር በመነጋገር የፍሳሽ መውረጃ ትቦ ውስጥ ገብተው ተጠርጣሪውን ለያዙት አባላት ማበረታቻና ሽልማት እንደሚሰጥም ማሳወቁን ፖሊስ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያሳያል።