AMN – ግንቦት 28/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመዲናዋን ነዋሪዎች የአገልግሎት አሰጣጥ ምሬት ለመቅረፍ የጀመረው ስር ነቀል የሪፎርም ጉዞ ውጤት እያፈራ ነው፡፡
በአስተዳደሩ ቁርጠኝነት ወደ ሥራ የገባውና ቀደም ሲል የነበረውን የተበታተነ፣ ጊዜ አባካኝ እና የሚታዩ የብልሹ አሰራር ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ የተወለደው አዲስ መሶብ ተቋማዊ አበርክቶው ከቀን ወደ ቀን እየላቀ መጥቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት የመንግሥት አገልግሎትን ማዘመን፣ ቢሮክራሲን ማቀላጠፍ እና የተገልጋዮችን አመኔታ መገንባት የከተማ አስተዳደሩ ቀዳሚ ተግባር ሆኗል።
ይህንን ታላቅ ራዕይ ሰንቀው የተነሱት የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በመዲናዋ የአገልግሎት አሰጣጥ ባህል ላይ መሠረታዊ እና ጉልህ ለውጦችን እያስመዘገቡ ይገኛሉ።

ከአዲስ መሶብ ምስረታ በፊት የነበረው አሠራር በተበታተነ ሒደት በከፍተኛ ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድና በጊዜ መባከን የተሞላ በመሆኑ የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴዎችን የሚያቀጭጭ ትልቅ ፈተና ነበር።
ግቡ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ተቋማትን አገልግሎት በአንድ ዲጂታል እና ማዕካላዊ መዋቅር ውስጥ በማቀናጀት ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊ፣ ዘመናዊ እና አስተማማኝ አገልግሎት ለነዋሪዎች ማቅረብ ነው።
በተለይም አቅመ-ደካሞችን፣ አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን ሰብአዊ ክብር በጠበቀ መልኩ ማገልገልንም ዓላማ አድርጓል።
የከተማ አስተዳደሩ በሰጠው ልዩ ትኩረት የአዲስ ሞሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎቱን ሲጀምር ከጥቂት ተቋማት ጋር የነበረ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፊ ተደራሽነትን መፍጠር ችሏል፡፡
በዚህም ከመጀመሪያው 18 ወደ 22 ተቋማት አድጓል።

በአሁኑ ወቅት የቋሚ ማዕከላት ቁጥር 8 የደረሰ ሲሆን ይህም በከተማ ደረጃ እቅድ የተያዘለትን የ11 ማዕከላት ግብ ለማሳካት የተደረገውን ስኬታማ ጉዞ ያሳያል።
ይህ ቴክኖሎጂ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት መካከል የመረጃ ልውውጥንም ያሳልጣል። ተገልጋዩ ሰነዶችን በተደጋጋሚ ለተለያዩ አካላት የመደጋገም ግዴታን በማስቀረት ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድን እጅግ ያቀላጥፋል።
ይህንን ዘመናዊ አሠራር በብቃት ለመምራት ማዕከላቱ የሰለጠነና ጠንካራ የሰው ኃይል መዋቅር ገንብተዋል።
ከቋሚ ማዕከላት ባለፈ አገልግሎቱን በቀጥታ ወደ ማህበረሰቡ መንደሮች ለማድረስ “የመሶብ ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ አገልግሎት” ሌላው ትልቅ የሪፎርም ርምጃ ነው።

ይህ በልዩ ሁኔታ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ሥርዓቶችን በመያዝ የተዋቀረው የመሶብ ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ አገልግሎት ራሱን የቻለ ተንቀሳቃሽ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በመሆን ማኅበረሰቡ ያለበት ቦታ ድረስ በመሄድ ሰብአዊ ክብርን የጠበቀና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
ይሄም አዲስ አበባን የዲጂታል እና የላቀ አገልግሎት ማዕከል ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ የጀመረው የሪፎርም ጉዞ አሁንም በላቀ ደረጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ማሳያ ነው ፡፡
በፍሬሕይወት ብርሃኑ