AMN ሰኔ 7/2018

የገዳ ስርዓት የዛሬውን ህያው ማህበራዊ ህይወትና የህዝቡን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚቀርጽ በመሆኑ ይበልጥ እንዲበለጽግና እንዲጠበቅ በትኩረት ይሰራል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

71ኛው የቱለማ ኦሮሞ ገዳ የስልጣን ርክክብ በሸገር ከተማ ዳካ ኮራ አርዳ ጂላ በድምቀት ተካሂዷል።
የሜልባ አባ ገዳ ጎበና ሆላ የስልጣን ዘመናቸውን አጠናቀው ለሙደና አባ ገዳ ጌቱ ተሊላ የስልጣን ርክክብ አድርገዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፤ የገዳ ስርዓት ለኦሮሞ ህዝብ አንድነት ዋነኛ መሠረት በመሆኑ፣እሴቶቹን ይበልጥ ማጠናከርና ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ባከናወነው የባህል ህዳሴ፣ ከዚህ ቀደም ተረስተውና ተጥለው የነበሩ የኦሮሞ ባህሎችና እሴቶች ዳግም እንዲያንሰራሩና እንዲገነቡ አድርጓል ብለዋል።

ይህንኑ ለማሳካትም ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ የገዳ ስርዓት በስርዓተ ትምህርት ውስጥ እንደ አንድ የትምህርት አይነት እንዲሰጥ መደረጉንና ትውልዱን በገዳ ስርዓት እሴቶች ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሩ በበኩላቸው፤ ቢሮው የኦሮሞን ታሪክ፣ ባህል፣ እሴትና ስነ-ምግባር ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት ቢሮው የአርዳ ጂላ (የባህልና ስርዓት ማከናወኛ) ቦታዎችን የማልማት እንዲሁም በገዳ ስርዓት ላይ ያተኮሩ የምርምርና ጥናት ስራዎች እንዲከናወኑ ሲያደርግ መቆየቱን ለአብነት ተናግረዋል።
አላንጌውን (የስልጣን በትሩን) ከተረከበው የቱለማ ገዳ ጋር በመሆንም የአርዳ ጂላ ቦታዎችን ከማልማት ጀምሮ ለኦሮሞ ገዳ ስርዓት እድገትና ልማት የሚበጁ ስራዎች እንደሚሰሩ ማስታወቃቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።