አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጥ ስትራቴጂካዊ የልማት ስራ ነው

AMN ሰኔ 9/2018 ዓ.ም

ግንቦት 2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ በግንባር ቀደምትነት የሚያስጠራት ታላቅ ሀገራዊ አጀንዳ ነው።

ይህ መርሃ ግብር በዋናነት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የደን ሽፋን ለመጨመር እና የተራቆቱ መሬቶችን ለመመለስ የተጀመረ ቢሆንም፣ ጥቅሙ ከኢኮሎጂካል ፋይዳው አልፎ ለሀገሪቱ የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ ቁልፍ ምሰሶ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ ጥበቃ እና የምግብ ሉዓላዊነትን በተግባር በማስተሳሰር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች እያስገኘ ይገኛል፡፡

ቀደም ሲል በአፈር መሸርሸር እና በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች አሁን ላይ እንደ አቮካዶ ፣ ማንጎ ፣ ፓፓያ እና ብርቱካን ያሉ ፍራፍሬዎች የሚመረቱባቸው ለም ስፍራዎች ሆነዋል።

አርሶ እና አርብቶ አደሩ ቀጥተኛ የምግብ ምንጭ እንዲያገኝ አስቸሏል ፣ ተጨማሪ ገቢ በመፍጠርም የዜጎችን የኑሮ አቅም አሳድጓል።

መርሃ ግብሩ ብዙ የፍራፍሬ እና ለምግብነት የሚውሉ ዛፎችን እንደ ቡና ፣ አቮካዶ እና ፓፓያ ያሉትን ያካተተ ነው።

ይህ አሰራር አርሶ አደሩ ከመደበኛው የሰብል ልማት ጎን ለጎን ምርቶችን እንዲያገኝ በማድረግ፣ የተለያዩ የፍራፍሬ አይነቶችን በቀጥታ ከእርሻ በማግኘት አመጋገብን እንዲያሻሽል እያገዘ ይገኛል ፣ ከተክሎች በሚገኝ ገቢም ኢኮኖሚያዊ አቅም እየተገነባ ነው፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለከብት መኖነት የሚያገለግሉ የዛፍ ዝርያዎችን በማስፋፋት፣ በድርቅ ወቅት የሚከሰትን የመኖ እጥረት በመቅረፍ የእንስሳት ሀብትን ለመጠበቅ ያስችላል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብቶች የአፈር፣ ውሃ እና ብዝሃ-ህይወት በዘላቂነት በመንከባከብ፣ ሀገሪቱ በራሷ አቅም የምግብ ፍላጎቷን እንድታሟላ እና ከውጭ ጥገኝነት እንድትላቀቅ እያደረገ ነው።

አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን የምግብ ነጻነት እና የዜጎችን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጥ ስትራቴጂካዊ የልማት ስራ ነው።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review