AMN- ሰኔ 11/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የከተማ አስተዳደሩን የ90 ቀናት የስራ ዕቅድን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት ከንቲባዋ፣ ዘንድሮ 6 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባን የደን ሽፋን 30 በመቶ የማድርስና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ዘንድሮም የተጠናከረ ስራ እንደሚከናወን ከንቲባ አዳነች አብራርተዋል፡፡
የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ስራ በተለይ ከኮፕ 32 ዓለም አቀፍ ጉባኤ ጋር ተያይዞ በስፋት እየተሰራበት መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ ለዚህም ዓላማ ብቻ ወደ 300 ሄክታር የሚጠጋ መሬት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ልማቱ ከተማዋን በዘላቂነት የመገንባት ፣ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ እና የስራ ዕድል የመፍጠር አቅም ያለው መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ ፣ የከተማ አስተዳደሩ እድሉን በመጠቀም ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ተመራጭ ለማድረግ ጠንክሮ እንደሚሰራ አብራርተዋል።
አስተዳደሩ እስካሁን ባቀዳቸው እቅዶች ውስጥ ያልተሳኩ ስራዎች አለመኖራቸውን የጠቆሙት ከንቲባዋ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርንም በተመሳሳይ ቁርጠኝነት እንደሚያሳካ መተማመናቸውን ገልጸዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ