የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ስኬታማነት የተቋም እና የግለሰቦች ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አጋር አካላት የጋራ ጥረት ውጤት ነው- ሜላትወርቅ ኃይሉ

AMN- ሰኔ 14/2018 ዓ.ም

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ስኬታማነት የተቋም እና የግለሰቦች ብቻ ሳይሆን፣ ድምጻቸውን የሰጡ ኢትዮጵያዊያን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ታዛቢዎች እና ሌሎች አጋር አካላት የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ማሳወቂያ መርሐ-ግብር እያካሄደ ይገኛል።

በመርሐ ግብሩ ንግግር ያደረጉት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፣ የምርጫው ስኬት የአንድ ተቋም ወይንም ግለሰቦች ስኬት አለመሆኑን ተናግረዋል።

ሰብሳቢዋ አክለውም፣ ለሰዓታት ድምጻቸውን ለመስጠት በትእግስት የጠበቁ በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ታዛቢዎች እና ሌሎች አጋር አካላት የጋራ ጥረት ውጤት ነው ብለዋል።

ስለዚህም ይህ መርሐ ግብር የምርጫ ውጤት ይፋ የሚደረግበት ብቻ ሳይሆን፣ የሁላችንንም የትብብር አቅም፣ ተቋማትን ማጽናት እና ማጠናከር አስፋላጊ መሆኑን ለማሳየት እና ለማጠናከር ያለመ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።

እንዲሁም የምርጫው ሂደት ከዲጂታል ምዝገባ እስከ የምርጫ ዝግጅት እና አፈጻጸም ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ብቻ መካሄዱን ተናግረዋል።

ይህም በተልይም በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በውጭ ሀገር ዜጎች የቴክኒክ ድጋፍ ሲስራ እንደነበር ገልጸው፣ አሁን ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ብቻ መሰራቱ የራስ አቅም ግንባታ ማሳያ ነው ብለዋል።

ሰብሳቢዋ አያይዘውም ለምርጫው ስኬት የተጉ አካላትን ያመሰገኑ ሲሆን፣ በተለይም የቦርዱ ሰራተኞች እና የምርጫ አጽፈጻሚዎች ለምጫው ስኬት ህይወት እስከመስጠት ላበረከቱት አስተዎጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review