የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት፤ የሕብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎና የበርካታ ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ነው- ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

AMN- ሰኔ 14/2018 ዓ/ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ያካሄደውን የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አጠቃላይ ውጤት ማሳወቂያ መርሐ-ግብር አካሂጿል።

በውጤት ማሳወቂያ መርሐ ግብሩ ላይ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ከተቋማዊ ነጻነት እስከ ቴክኖሎጂ ሽግግር የተመዘገቡ ስኬቶችን አስመልክቶ አብራርተዋል።

ቦርዱ በምርጫው ሂደት ተቋማዊ ገለልተኝነቱን ጠብቆ፣ አካታችነትን መርህ በማድረግ በሕግና በመመሪያ መሠረት ብቻ ውሳኔዎችን ማሳለፉንና ሥራዎቹን ማከናወኑንም ገልጸዋል።

ቦርዱ ከማንኛውም የፖለቲካ ጫናና ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆኖ ሥራውን በስኬት ማጠናቀቁንም ተናግረዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በወጣት ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በለማ ሲስተም የዲጂታል የእጩዎችና የመራጮች ምዝገባ መካሄዱንም አውስተዋል።

መራጮች ወደ ጣቢያ ሳይሄዱ ባሉበት ሆነው እንዲመዘገቡ ያስቻለው ይህ ቴክኖሎጂ፣ ተቋሙን ከውጭ ድርጅቶች ጥገኝነት ነጻ ያደረገ ትልቅ የእውቀት ሽግግር ማሳያ ሆኗል ብለዋል።

በተጨማሪም ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀናጀ የምርጫ ሥራ ማስፈጸሚያ መመሪያ ማዘጋጀት፣ እንዲሁም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል አስፈጻሚ ግብረ ኃይልና ጾታዊ ትንኮሳን መከላከያ ፖሊሲ በተግባር ላይ መዋሉንም ገልጸዋል።

የምርጫው ስኬት የሕብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎና የበርካታ ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ውጤት መሆኑንም ነው ሰብሳቢዋ የገለጹት።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review