ከሚሰራበት ድርጅት ውስጥ ተሽከርካሪ በመሰወርና አካሉ እንዲበተን ያደረገ ተጠርጣሪ ከነግብረ አበሮቹ በቁጥጥር ስር ዋለ

AMN- ሰኔ 17/2018 ዓ.ም

አበራ መረሳ የተባለው ተጠርጣሪ ወንጀሉን የፈፀመው ሰኔ 5 ቀን 2018 ዓ/ም በአሽከርካሪነት ተቀጥሮ ከሚሰራበት ቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ስታዲየም አካባቢ ከሚገኝ አንድ የኮንስትራክሽን ድርጅት ነው፡፡

ተጠርጣሪው ወንደሠን አባተ፣ ሶይብ ሙኒር፣ ክንዱ ደጉ፣ ስንታየሁ ተመስገንን፣ ብሩክ ግርማ፣ ባህሉ ሲሳይ ከተባሉ አባሪዎቹ ጋር በመመሳጠር ግምቱ 18 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አ/አ 48 4 05 HILUX ፒካፕ ተሽከርካሪን ከድርጅቱ ይዞ በመውጣት ከአንድ ግለሰብ ጋር በ 6መቶ ሺ ብር ለመሸጥ ተስማምቷል።

ግለሰቡ ቀደም ብሎ የሽያጩን ቀብድ 110 ሺህ ብር በመቀበልና ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን አዳማ ከተማ ላይ የተሽከርካሪውን አካል በመነቃቃልና በመበታተን በአንድ መጋዘን ውስጥ አስቀምጧል፡፡

የወንጀል ድርጊቱን ሲያጣራ የነበረው በቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ የአደይ አበባ ስታዲየም አካባቢ ፖሊስ መምሪያ ሲሆን ሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ/ም ከሀገር መከላከያ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት እንዲሁም ከአዳማ ከተማ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በወንጀሉ ተሳታፊ የሆኑ በአጠቃላይ 7 ተጠርጣሪዎችን ከነ ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሊያውልም መቻሉን መምሪያው ለኤ ኤም ኤን የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡

የመንግስትም ሆነ የግል ድርጅቶች ሠራተኞችን ሲቀጥሩ የሠራተኞቻቸውን ማንነት የሚገልጽ አስፈላጊ ሠነዶች አሟልተው መሆን እንዳለበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ መልዕክቱን አስተላልፏል።

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review