በኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር ማዕቀፍ ኢትዮጵያ እና ኒውዚላንድ የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ስምምነት ተፈራረሙ

You are currently viewing በኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር ማዕቀፍ ኢትዮጵያ እና ኒውዚላንድ የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ስምምነት ተፈራረሙ

AMN ሰኔ 18/ 2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገው የድርድር ሒደት አካል የሆነውን የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ፕሮቶኮል ከኒውዚላንድ ጋር ተፈራረመች።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ ወደ ዓለም አቀፉ የባለብዙ ወገን የንግድ ሥርዓት ለመቀላቀል ለምታደርገው ጉዞ ትልቅ ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑ ተገልጿል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ለረጅም ጊዜ ሲካሔድ የነበረውን የሁለትዮሽ ድርድር ያጠናቀቀው ይህ ስምምነት፣ በሸቀጦችና በአገልግሎት ዘርፎች ላይ በጋራ የተደረሱ የገበያ ተደራሽነት ግዴታዎችንና ጥቅሞችን ያካተተ ነው።

ፕሮቶኮሉን በጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ቋሚ መልዕክተኛ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አምባሳደር ፀጋአብ ከበበው እና በዓለም ንግድ ድርጅት የኒውዚላንድ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ክሌር ኬሊ ፈርመውታል።

ይህ ስምምነት ሁለቱ አገራት ግልጽነት የሰፈነበት፣ በሕግ የሚመራ እና ልማትን ማዕከል ያደረገ የባለብዙ ወገን የንግድ ሥርዓት ለመገንባት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ መሆኑ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተመላክቷል።

የኒውዚላንድ ቋሚ መልዕክተኛ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ የምትገኝ አገር መሆኗን በማንሳት የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ስትሆን ከሌላው ዓለም ጋር የሚኖራትን የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር ዕድል እንደሚሰጣት ገልጸዋል።

አያይዘውም አገራቸው የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደት በመደገፍ ረገድ የምታደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀዋል። በተጨማሪም ስምምነቱ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር የተሻለ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ከበበው በበኩላቸው በድርድሩ ሒደት ሁሉ ኒውዚላንድ ላሳየችው ገንቢ ተሳትፎ እና ቀጣይነት ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ከሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነቱ ባለፈ፣ ኢትዮጵያ እና ኒውዚላንድ በተለያዩ ዓለም አቀፍና ባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ያላቸውን የቅርብ ትብብር አጠናክረው ቀጥለዋል።

በኒውዚላንድ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት እያደገ የመጣ ሲሆን፣ ግንኙነቱ በዋናነት በግብርና ትብብር፣ በጂኦተርማል (የእንፋሎት) ኃይል ድጋፍ እና በቴክኒክ አገልግሎቶች ላይ ያተኮረ መሆኑን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review