በተግባር የተሰበረ ተስፋ መቁረጥ፤ ‘ብንደመርና ብንተጋገዝ ውብ ሀገር አለን’- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing በተግባር የተሰበረ ተስፋ መቁረጥ፤ ‘ብንደመርና ብንተጋገዝ ውብ ሀገር አለን’- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሰኔ 22/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያውያን ተባብረውና ተደምረው ከሰሩ ተስፋ አስቆራጭ ድምጾችን በስራ መስበርና ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እንደሚችሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማትን መርቀው ባስተላለፉት መልዕክት፣ መቆሸሽ፣ መጠልሸት፣ ማነስና በሌላ ቦታ እየሄዱ መቅናት ለኛ አይገባንም ብለዋል።

አዲስ አበባንና ኢትዮጵያን የመለወጥ ጉዞ በፈተናዎችና በተስፋ መቁረጥ ድምጾች የታጠረ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።

ስራዎች ሲጀመሩ ከግራና ከቀኝ፣ ጠዋትና ማታ “አትችሉም፣ አይሳካላችሁም፣ አታከናወኑም፣ ትጀምራላችሁ እንጂ አትጨርሱም” የሚሉ በርካታ የውስጥና የውጭ ድምጾች ይሰሙ እንደነበር ጠቁመው ምላሹ ግን በተግባር መስራት መሆኑን ገልጸዋል።

የኛዎቹ ይገርመኛል፣ ሌሎቹ ግን አይገባችሁም እያሉን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የለም፣ ይገባናል! የለም፣ እንችላለን! ጥንታውያን ነበርን፣ በመሃል ጠፍተን ሊሆን ይችላል፣ ብንሰናሰል፣ ብንደመር፣ ብንተጋገዝ ውብ ሀገር አለን ብለዋል።

ከማናችሁም የማያንስ ኢኮሎጂ እኛም ተሰጥቶናል ብለን መናገር ብቻ አይደለም፣ ሰርተን ማሳየት አለብን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይህ ስራ ሲጀመር በአካባቢው ልማቱን ለማስተጓጎል የሞከሩና ያስቸገሩ ኃይሎች እንደነበሩ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ ዛሬ ግን እነዚያው አካላት የፕሮጀክቱ ዋና አድናቂዎችና ቀዳሚ ተጠቃሚዎች መሆን መቻላቸውን በምሳሌነት አንስተዋል።

ዐይናችን ግንባር እንዳይሆን፣ ዐይናችን ዐይን እንዲሆን ሀገራችንን ማየትና አብልጦ መስራት የሚቻል ነገር እንደሆነ አንዱ ማሳያ ቀበና ነው ሲሉ ልማቱ የዕይታንና የማሰብን አድማስ የቀየረ መሆኑን አስረድተዋል።

ዜጎችና የከተማዋ ነዋሪዎች አዲሱን የወንዝ ዳርቻ ልማት እንዲያዩና እንዲዝናኑበት ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላየነውን እዩ፣ ያልሰራነውን ስሩ፣ አልቃችሁ አሳምሩና ለልጆቻችን በረከትና ሀብት አድርጉላቸው በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review