በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሰኔ 27/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ እያንሰራራችና ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆኑ የብልጽግና ጉዞዎችን እያከናወነች መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ሀገር ወዳጆች ውብና እንግዳ ተቀባይ ወደሆነችው የአርባ ምንጭ ከተማ በመምጣት ዕድገቱን እንዲመለከቱና ደስታውንም እንዲጋሩ ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት ምረቃ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻነቷ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ የኢንቨስትመንትና የንግድ ሀሳቦች የሚመነጩባት ትልቅ የዕድገት ማዕከል መሆንዋን ገልጸዋል።

በተለይም በቅርቡ በከተማዋ የተመለከቱትን የሐር ምርት ሥራ በማሳያነት በመጥቀስ፤ አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ በዘርፉ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር መዋዕለ-ነዋይ (ኢንቨስትመንት) ለማፍሰስና ምርቱን ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ መነሳሳቱን አውስተዋል።

«ሰው ወደ ከተማዋ ሲመጣ ለመዝናናት ብቻ አይመጣም፤ ወይ እውቀት ያካፍላል፣ ወይ ገንዘብ ያፈስሳል፣ አልያም አዳዲስ የኢንቨስትመንት ሀሳቦችን ያመነጫል» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመሆኑም የሚመጡ እንግዶችን በታላቅ ክብርና በመልካም ስነ ምግባር ማስተናገድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አክለውም፤ በያዝነው ዓመት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ 10 ነጥብ 2 በመቶ በሆነ የኢኮኖሚ ምጣኔ የምታድግ ብቸኛ ሀገር መሆንዋን አስታውቀዋል።

ይህ ዕድገት በወረቀት ላይ ብቻ ያለ ሳይሆን በተለያዩ ከተሞች የሚከናወኑትን የልማት ጅማሮዎች ማየት በቂ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሀገሪቱ እያማረባትና በሁሉም መመዘኛዎች እያንሰራራች መሆኑን ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አሁን ላይ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ማሰብ የሚጀምሩበት ምቹ ጊዜ ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

በመጨረሻም፣ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ወደ ኋላ ለመጎተት የሚፈልጉ ኃይሎች ቢኖሩም፤ ልማትን፣ ሰላምንና ብልጽግናን የሚያስቡ ዜጎች ግን በትጋትና በሥራ እያሸነፉ ጉዟቸውን ወደ ፊት እንደሚያደርጉ የጸና እምነት እንዳላቸው አስገንዝበዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review