ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከመንግሥት ድጋፍ ባለፈ የሁሉንም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ እገዛና ትብብር ይሻሉ- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ

You are currently viewing ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከመንግሥት ድጋፍ ባለፈ የሁሉንም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ እገዛና ትብብር ይሻሉ- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ

AMN – ሰኔ 27/2018 ዓ.ም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ በተካሄደው የሀዋሳ የሐይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የአጋርነት መድረክ ላይ በመገኘት ይህንን ትልቅ ሀገራዊ ራዕይ የመጋራት ዕድል አግኝቻለሁ ብለዋል።

ሀዋሳ ማራኪ ሐይቋን ጨምሮ ልዩ ተፈጥሯዊ ጸጋዎች የተቸሯት ከተማ ናት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን፣ ይህንን ስጦታ መጠበቅና ማልማት የጋራ ታሪካዊ ኃላፊነታችን ነው ብለዋል፡፡

የተጀመረው የሐይቅ ዳርቻ ልማት የውበት ሥራ ብቻ ሳይሆን ሰፊ የቱሪዝም፣ የኢኮኖሚ፣ የሥራ ፈጠራና የአካባቢ ጥበቃን ያቀፈ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ታላላቅ ፕሮጀክቶች በመንግሥት ጥረት ብቻ ሊሳኩ ስለማይችሉ የሕዝባችን፣ የግሉ ዘርፍ፣ የምሁራንና የዳያስፖራው ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ ነው። ለሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት የሚደረገው ድጋፍ ከገንዘብ ባሻገር እውቀትን፣ ልምድንና በጎ ተጽዕኖን ማካተት ይኖርበታል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የከተማዋን የመዝናኛ፣ የንግድና የመኖሪያ ሥፍራነት ወደ ላቀ ምዕራፍ በማሸጋገር ሀዋሳን በምስራቅ አፍሪካ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ያደርጋታል።

ለዚህ ትልቅ ራዕይ መሳካት እያንዳንዱ ዜጋ በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በጉልበቱ የሚያበርክተው አስተዋፅዖ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በመልዕክታቸው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review