AMN- ሐምሌ 05/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል፡፡
በጉባዔው ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአስተዳደራቸውን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፣ በተለይም የከተማዋን የውሃ አቅርቦት በተመለከተ በዝርዝር ሪፖርት አቅረበዋል፡፡
ከንቲባዋ በሪፖርታቸውም በ2013 በጀት ዓመት ማብቂያ በቀን 570ሺህ ሜትር ኪዩብ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ የውሃ ምርት አቅም፣ አሁን ላይ ወደ 850ሺህ ሜትር ኪዩብ በቀን ማሳደግ ተችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቀን 280ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ የማምረት አቅም ተፈጥሯል።
የከተማዋን የውሃ አቅርቦት ሽፋን በበጀት ዓመቱ ማብቂያ በቀን በ60 ሺህ ሜ.ኩብ ለማሳደግ እስከ 20 የሚደርሱ አዳዲስ ጥልቅ ጉድጓዶች ተቆፍረው ወደ ስርጭት መግባታቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል፡፡

በቀን 100ሺህ ሜትር ኩብ ውሃ ማምረት ከሚያስችለው የጭቋላ ዌል ፊልድ የውሃ ልማት ፕሮጀክት ጋር የተቆፈሩ ጉድጓዶችን ወደ ስርጭት ለማስገባት የግንባታ ሥራው 30 በመቶው ደርሷል። በሌላ በኩል በቀን እስከ 73 ሺህ ሜትር ኩብ ውሃ መስጠት የሚያስችለው የገርቢ መጠጥ ውሃ ግድብ ግንባታ መጀመሩንም በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡
አንጋፋው የለገዳዲ የውሃ ግድብ እድሳትና ማሻሻያ ተደርጎለት ለተጨማሪ 50 ዓመታት እንዲያገለግል የማስቻል ሥራ ተከናውኗል።
የዘመናዊ ፍሳሽ ማስወገድ ሥርዓት ሽፋን ከ36 በመቶው ወደ 42 በመቶው ያደገ ሲሆን፥ በከተማዋ የነበረው የፍሳሽ ማጣሪያ ከአንድ ወደ 44 ማጣሪያዎች ከፍ እንዲል ተደርጓል።
በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ከ60 በመቶው በላይ ማደጉን እና የዘመናዊ ፍሳሽ አወጋገድና ማጣራት ሥርዓት በከፍተኛ ደረጃ መሻሻሉን ከንቲባዋ ገልፀዋል፡፡

እንዲሁም ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ሽፋን ለማሳደግ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የገለፁት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የተከናወኑ የመንገድ ግንባታዎች የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ አሻሽለዋል ብለዋል፡፡
በዚህም በአምስት ዓመታት ውስጥ ከ1ሺህ 600 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ የተገነባ ሲሆን፣
የከተማዋን የመንገድ ሽፋን ከነበረበት የ12 በመቶው ምጣኔ ወደ 20 በመቶው ማሳደግ መቻሉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለምክር ቤቱ በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡
በያለው ጌታነህ