በህገ-ወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩ 24 ሺህ 568 የንግድ ድርጅቶች ላይ የእርምት እርምጃ ተወስዷል

You are currently viewing በህገ-ወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩ 24 ሺህ 568 የንግድ ድርጅቶች ላይ የእርምት እርምጃ ተወስዷል

AMN – ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድ አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና በዘርፉ የሚስተዋሉ ቢሮክራሲያዊ አሠራሮችን ለመቀየር ባከናወናቸው የተቀናጁ ስትራቴጂካዊ ሥራዎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ ይህንን የገለጹት የከተማ አስተዳደሩን የ2018 ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት ነው።

እንደ ከንቲባዋ ማብራሪያ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በንግድ ሥርዓቱ ላይ የነበረውን ቢሮክራሲያዊ አሠራር በመቀየር ሂደቱን ቀላል በማድረግ ከ270 ሺህ በላይ አዳዲስ ነጋዴዎች ወደ ንግድ ሥርዓቱ እንዲቀላቀሉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አብራርተዋል፡፡

የንግድ ድርጅቶች ሕጋዊነትን ከማረጋገጥና የሕገ-ወጥ ንግድ እንቅስቃሴዎችን ከመግታት አኳያ ሰፊ የክትትል ሥራ መከናወኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በአጠቃላይ በ231 ሺህ 828 የንግድ ተቋማት ላይ የበር ለበር ክትትል የተደረገ ሲሆን፣ ሕገ-ወጥ ሆነው በተገኙ 24 ሺህ 568 ድርጅቶች ላይ የእርምት እርምጃ መወሰዱንም ከንቲባዋ በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡

የእርምት እርምጃ ከተወሰደባቸው ተቋማት መካከል 20 ሺህ 617 ነጋዴዎች የአሠራር ማስተካከያ በማድረግ ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል ከንቲባ አዳነች።

በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና የንግድ ተቋማት ያላቸውን የመወዳደርና የምርት አቅርቦት አቅም ለማሳደግ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎች ተወስደዋል።

የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠርና የንግድ አቅምን ለማጠናከር የከተማዋ የንግድ ኮርፖሬሽን ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ መነሻ ካፒታል ይዞ እንዲቋቋም መደረጉም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

የሕብረት ሥራ ማኅበራት ካፒታል በዕቅድ ከተያዘው በላይ በ3.5 ቢሊዮን ብር ያደገ ሲሆን፣ አጠቃላይ ቁጠባቸውም 8.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ በተጨማሪም ለማኅበራቱ አባላት 7.1 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ብድር ማቅረብ እንደተቻለም አብራርተዋል፡፡

ከሕጋዊ አሠራር ውጪ በሚንቀሳቀሱና የንግድ ሥርዓቱን በሚያስተጓጉሉ አካላት ላይ ጥብቅ የኢንስፔክሽን ሥራ መከናወኑንም ከንቲባዋ በሪፖርታቸው አስረድተዋል።

በተደረገው የኢንስፔክሽንና የክትትል ሥራ ሕግን ተላልፈው በተገኙ 500 የሕብረት ሥራ ማኅበራት እንዲሁም 633 አመራሮችና ሠራተኞች ላይ አስተዳደራዊ የማስተካከያ እና የገንዘብ ቅጣት እርምጃ ብለዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review