AMN – ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም
ባለፉት አምስት ዓመታት በታቀደው ልክ የተሳኩት ሥራዎች የሚያበረታቱ ቢሆኑም፣ ከዚህ በላይ መሥራትን እንደሚጠይቅ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።
አቶ ጃንጥራር አባይ በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከምክር ቤት አባላት በፍትህ ሥርዓቱ እና በኑሮ ውድነት ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
በምላሻቸውም ቀደም ሲል በነበረው ታሪክ፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል በሚደረግ የፍትህ ክርክር መንግሥት የሚሸነፍበት ሁኔታ እንደነበርና አሁን ላይ ይህንን የቀየረ ትልቅ ስኬት መመዝገቡን አንስተዋል።
መንግሥት ትክክለኛውን የሕግ ሥርዓት ተከትሎ በመክሰስ ማሸነፍ በመቻሉ ብዙ ሀብት እንዲመለስ ያደረገ ትልቅ ለውጥ መምጣቱን በመግለጽም፣ ጉዳዮችን በክርክር፣ በድርድርና በእርቅ በመጨረስ የመንግሥት ሀብት እንዳይባክን እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከከተማዋ ቻርተር ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ ሲመልሱም፤ ሰነዶች ተዘጋጅተው የቆዩ ቢሆንም፣ በፌደራል ደረጃ ታይተው ሳይጸድቁ የቆዩት ከሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አጀንዳዎች ጋር ጎን ለጎን ማየት ስለሚያስፈልግ እንደሆነና ከምክክር ኮሚሽኑ ውጤት ጋር ተያይዞ የሚጸድቅበት ሁኔታ ታሳቢ መደረጉን አመላክተዋል።
የኑሮ ውድነትን ችግር ለመቅረፍም ጉዳዩ በትኩረት ታይቶ ሰፊ የከተማ ድጎማዎች እየተደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ከእነዚህም መካከል የጤና መድህን፣ የትራንስፖርት ድጎማ፣ የምገባ ማዕከላት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የቤት ልማት እና የአገልግሎት አሰጣጥን የማሳለጥ ተግባራት ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።
ከተማዋ አብዛኛውን የግብርና ምርት ከክልሎች የምታገኝ በመሆኑ፣ ነዋሪዎችን ለመደገፍ የቅዳሜና እሑድ ገበያዎችንና የገበያ ማዕከላትን የማስፋፋት ሥራ መቀጠሉንም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የንግድ ሥራ ድርጅቶች፣ ማኅበራትና የገበያ ማዕከላት ምርት ክምችት ስላላቸው ገበያውን ለማረጋጋት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

በተለይም በ2018 በጀት ዓመት በሀገር ውስጥ በሚመረቱ እንደ ዱቄት፣ ዳቦ፣ ፓስታና ማካሮኒ ባሉ የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ሰፊ የዋጋ ንረት አለመታየቱን አብራርተዋል።
ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን በቅዳሜና እሑድ ገበያ እያቀረቡ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው፣ ምርታማነታቸውን ለመጨመር የመብራት፣ የውሃ፣ የመንገድ አገልግሎት እና የገበያ ትስስር ችግሮቻቸው እየተፈቱላቸው እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በአንጻሩ በተወሰነ ደረጃ የዋጋ ንረት የታየው ከውጭ በሚገባው የዘይት ምርት ላይ ብቻ እንደሆነም ነው ያብራሩት።
በታምራት ቢሻው