የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባለፉት አምስት ዓመታት 18 አዳዲስ አዋጆችንና ደንቦችን አውጥቷል

You are currently viewing የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባለፉት አምስት ዓመታት 18 አዳዲስ አዋጆችንና ደንቦችን አውጥቷል

AMN – ሐምሌ 6/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል፡፡ ምክር ቤቱ በሁለተኛ ቀን ውሎው የምክር ቤቱ እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት አዳምጧል፡፡

የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ፋዒዛ መሐመድ፤ ምክር ቤቱ ባለፉት አምስት ስትራቴጂካዊ የልማት ዓመታት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት አፈጻጸም በሪፖርት አቅርበዋል፡፡

በቀረበው ሪፖርት መሰረት ምክር ቤቱ የህግ ማውጣት ስልጣኑን በመጠቀም ለከተማዋ ሁለንተናዊ ልማትና ዘመናዊነት የሚያግዙ 10 አዳዲስ አዋጆችን እና 6 አዳዲስ ደንቦችን ያወጣ ሲሆን፤ በአፈጻጸም ሂደት ላይ ያጋጠሙ የአሰራር ማነቆዎችን በፍጥነት ለመፍታትም በ8 ነባር አዋጆችና በ2 ደንቦች ላይ ማሻሻያ ማድረጉ ተመላክቷል፡፡

በተለይም የበጀት አዋጆች በወቅቱ መጽደቃቸው ድህነት ተኮር የሆኑ የልማት ስራዎች ሳይዘገዩ እንዲከናወኑና ህዝቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ማስቻሉን ምክትል አፈ ጉባኤዋ በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

በክትትልና ቁጥጥር ረገድ፣ ምክር ቤቱ በአደረጃጀትና በአሰራር ደንቡ መሰረት በአስፈጻሚ አካላት ላይ በዓመት 4 ጊዜ መደበኛ የሱፐርቪዥን የመስክ ምልከታ እንዲሁም በዓመት በአማካይ 2 ጊዜ ድንገተኛ የመስክ ምልከታዎችን ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውቀዋል።

ይህም የህዝብ አንገብጋቢ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች በአንድ ማዕከል ተሰብስበው ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙና ብልሹ አሰራሮች ወደ ብክነት ሳይመሩ በፊት እንዲታረሙ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉ በሪፖርቱ ተገልጿል።

የህዝብ ውክልናን ከማረጋገጥ አንጻርም በ10 የምርጫ ክልሎች (ክፍለ ከተሞች) ውስጥ የከተማ ምክር ቤትና የፓርላማ አባላትን ያቀፈ ጠንካራ የመራጭ-ተመራጭ ትስስር አደረጃጀት በመፍጠር፣ በድምሩ 20 ጊዜ የተዘጋጁ መድረኮች መካሄዳቸውን ሪፖርቱ ያሳያል።

በእነዚህ መድረኮች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን የተነሱት ጥያቄዎች በየደረጃው ምላሽ እንዲያገኙና አስፈጻሚው አካል በጉባኤ ላይ ቀርቦ ማብራሪያ እንዲሰጥ መደረጉን ምክትል አፈ ጉባኤዋ በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡

ምክር ቤቱ የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማሳደግ ከከተማ እስከ ወረዳ ድረስ አባላቱን በኮከስ በማደራጀት በሰላምና በልማት ስራ ላይ እንዲሳተፉ ያደረገ ሲሆን ተቋማዊ ሪፎርም በማካሄድም አደረጃጀቱን፣ አሰራሩንና የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ በማዘመን ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠሩንም ገልጸዋል፡፡

በተያያዘም የፍትህና ዳኝነት አካላት የህዝብ አመኔታን ያተረፈ ፈጣን አገልግሎት እንዲሰጡ የትራንስፎርሜሽን ስራዎችን ያስተባበረው ምክር ቤቱ፣ በውጭ ግንኙነት ዘርፍም ከብራዚል፣ ከደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ከብሪክስ ሀገራት ምክር ቤቶች ጋር የአጋርነትና የጋራ ግብ ስምምነቶችን በመፈራረም ወደ ስራ መግባቱን በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review