ሀገራዊ ምክክሩ የታሪክ ስብራታችንን ለመጠገን ወሳኝ መፍትሔ ነው

AMN – ሐምሌ 9/2018 ዓ.ም

ሀገራዊ ምክክሩ የታሪክ ስብራታችንን ለመጠገን ወሳኝ መፍትሔ ነው ሲሉ የሰላምና ደኀንነት መምህርና ተመራማሪ አሌክስ ብርሃኑ ገለጹ፡፡

በሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማስጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ከብት ሲገዛ ብር ያላዋጡ ከብቱ ሲታረድ ግን ያንዣብባሉ” በማለት የተናገሩት፤ የኢትዮጵያን የውስጥ ተጋላጭነት ተከትለው ብሔራዊ ጥቅሟን ለመጋራት አድፍጠው የሚጠብቁ የውጭ ኃይሎችን የሚገልጽ መሆኑን ተመራማሪው ጠቁመዋል።

በታሪካችን የውስጥ አለመረጋጋት የውጭ ወረራንና ጥቃትን እንደሚጋብዝ በተደጋጋሚ መታየቱንም አውስተዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት በባለቤትነት ስትጠቀምበት የነበረውን የባሕር በር በፖለቲካ ሸፍጥና በወቅቱ በነበረ የውስጥ ድክመት ምክንያት እንድታጣው መደረጉን ጠቁመው ፤ የውስጥ ጥንካሬ ቢኖር ኖሮ ዛሬ ውይይታችን ስለ ወደብ ባለቤትነት ሳይሆን ወደቡን ለዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ተጽዕኖ እንዴት እንደምናውለው ይሆን ነበር ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ እስካሁን የነበሩ የፖለቲካ ለውጦች ሁሉ በንጉሡ፣ በደርግና በኢህአዴግ ዘመን በኃይለ ቃል ተጀምረው በጦር መሣሪያና በኃይል የተጠናቀቁ ፣ ችግሮችን በዘላቂነት ከመፍታት ይልቅ አዘግይተው የሚያልፉ እንደነበሩ አንስተዋል።

በአንጻሩ አሁን እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር ከፖለቲካ ልሂቃን ቁጥጥር ወጥቶ፣ ሕዝቡ ተወያይቶ “ችግሬ ይህ ነው” ብሎ ያቀረበበትና የታሪክ ስብራቶችን ለመጠገን የሚያስችል ታሪካዊ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ ሂደት መጪው ትውልድ ከተለመደው የ”እኛ እና እነሱ” ክፍፍል ወጥቶ የጋራ ራዕይ እንዲኖረው የሚያስችል ወሳኝ መሠረት እንደሚጥልም ነው ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያውያን በሰፈርና በትንንሽ ጉርሻዎች ሲጣሉ ትልቁን መሶብ የሚቀማ የውጭ ኃይል በቀጣናው አድፍጦ ይጠብቃል ያሉት ተመራማሪው፤ ነገር ግን በአንድነት ሲቆሙ እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚችሉ በተግባር አሳይተዋል ብለዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review