AMN – ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ በትምህርት ተደራሽነትና ፍትሐዊነት ላይ የተጣለውን ግብ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት፣ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ማዕከላት ቁጥርን 124 ማድረስ ተችሏል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን 34 ሺህ 117 ተማሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ የልዩ ፍላጎት ማዕከላትን ቁጥር ወደ 124 ማሳደጉን ቀደም ባሉት ይፋዊ መግለጫዎች አረጋግጧል።
የማዕከላቱን ቁጥር ከፍ ከማድረግ ባለፈ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ምቹና ቀልጣፋ የመማር ማስተማር ሂደትን ለመፍጠር የሚያስችሉ ዘመናዊ የትምህርት ግብዓቶች እንዲሟሉ ተደርጓል፡፡
ይህ የተደራሽነትና የጥራት ማሻሻያ ሥራ በከተማዋ የሚገኙ ሁሉም ሕፃናትና ታዳጊዎች ያለ ምንም ልዩነትና አድልዎ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ለማስቻል የተጀመረው ሰፊ ስትራቴጂ አካል ነው፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ሥር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተቋቋሙት ማዕከላት ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ የፍትሐዊነት መጥበብና የግብዓት እጥረትን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀርፉ ናቸው፡፡
ማዕከላቱ የተለያየ ጉዳት ያለባቸውን ተማሪዎች ፍላጎት ማዕከል ባደረገ መልኩ የተደራጁ ሲሆን ለሒደቱ ስኬታማነትም ዘመናዊ የብሬል መጻሕፍት፣ የድምፅ ማጉያ መሣሪያዎች፣ ልዩ የሥነ-ልቦና ማገገሚያ ቁሳቁስ እና የመማሪያ ቴክኖሎጂዎች እንዲሟሉ ተደርጓል።
ይህም የተማሪዎችን የመማር ተነሳሽነት በማሳደግ ረገድ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ይስተዋሉ የነበሩ ተያያዥ ተጽዕኖዎችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባሳለፍነው እሁድ በተካሄደው የምክር ቤት ጉባኤ የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የኦዲት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፤ የትምህርት ግብዓትን ከማሟላት ጎን ለጎን ማዕከላቱን በዕውቀትና በክህሎት የሚመሩ ባለሙያዎችን የማሟላት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች በልዩ ሁኔታ መደገፍና ማስተማር የሚችሉ መምህራንን በየማዕከላቱ መመደባቸው የትምህርት ጥራቱን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ተግባር ሆኗል።

ይህ በትምህርት ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ስኬት በከተማዋ ማኅበራዊ ፍትሕን ለማረጋገጥና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ ለታለመው ግብ ትልቅ ማሳያ ነው።
በቀጣይም የማዕከላቱን ቁጥር ይበልጥ በማሳደግና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የማስተዋወቅ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።
በወርቅነህ አቢዮ