AMN- ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም
አዲሱ የመረጃ ነፃነት አዋጅ የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት ለማስጠበቅ እና ግልጽነትን ለማስፈን ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ያፀደቀውን የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 1427/2018 አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም አዲሱ አዋጅ የዜጎችን መረጃ የመጠየቅና የማግኘት መብት በአግባቡ እንዲከበር ከማስቻሉ በላይ ቀደም ሲል በነበሩ የሕግና የአፈጻጸም ክፍተቶች ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ብለዋል።
ከ17 ዓመታት በላይ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የቀድሞው አዋጅ ሀሳብን የመግለጽ እና የመረጃ የማግኘት ነጻነትን በአንድ ላይ አጣምሮ በመያዙ በአፈጻጸም በኩል በርካታ ተግዳሮቶች እንደነበሩበት አስታውሰዋል፡፡
አዲሱ አዋጅ በ7 ክፍሎች፣ በ60 አንቀጾች እና በ197 ንዑስ አንቀጾች የተደራጀ ሲሆን ዘመናዊ የሰብአዊ መብት ጽንሰ-ሐሳብንና የቴክኖሎጂ ዕድገትን የተከተለ መሆኑን አስረድተዋል።
አዋጁ የመረጃ ነፃነት አፈጻጸምን ውጤታማ ለማድረግ በርካታ ድንጋጌዎች መያዙን ጠቅሰው የሕጉ ተፈጻሚነት ከመንግስት ተቋማት በተጨማሪ፣ ከመንግስት ጋር የገንዘብ ትስስር ያላቸውን፣ መንግስታዊ ሥራ የሚያከናውኑትንና የመንግስት ድርሻ ያላቸውን የግል ተቋማትም ያካትታል ብለዋል።
በእያንዳንዱ ተቋም ውስጥ ግልጽ የአሰራር ሥርዓት የመዘርጋት ኃላፊነት የተቋማቱ የበላይ ኃላፊዎች ሃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው መረጃ በሰነድ ባይደራጅም እንኳ በቃል እንዲሰጥ ከተጠየቀ የመስጠት ግዴታ እንደተጣለበትም ጠቅሰዋል፡፡
ተቋማት መረጃዎችን በፍጥነት መስጠት የሚያስችል ዘመናዊና በኮምፒውተር የታገዘ የሰነድ አያያዝ ሥርዓት የመዘርጋት ግዴታ እንዳለባቸው መደንገጉን ዋና ዕንባ ጠባቂዋ ስመኝ ውቤ እንደገለጹ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የዜጎችን መብት ለማስከበር የመረጃ ጥያቄ ምላሽ መስጫ ጊዜያት በአዋጁ እንዲያጥሩ መደረጉን ጠቅሰው መደበኛ የመረጃ ጥያቄ ከ30 ቀናት ወደ 21 የሥራ ቀናት ዝቅ ተደርጓል፣ ለአንድ ጊዜ ብቻ ለ14 ቀናት ሊራዘም ይችላል ብለዋል።
የአስቸኳይ መረጃ ጥያቄዎችም ከ10 ቀናት ወደ 48 ሰዓታት ዝቅ እንዲል መደረጉን በመግለጽ አዋጁ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ልዩ የሕግ ከለላ መስጠቱን ዋና ዕንባ ጠባቂዋ ስመኝ ውቤ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ይህንን አዋጅ በአግባቡ ለማስፈጸም ሰፊ የክትትል፣ የማስፈጸም፣ አስተዳደራዊ እርምጃ የመውሰድና ስልታዊ ምርመራዎችን የማካሄድ ሥልጣን እንደተሰጠው ገልጸዋል።