AMN – ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም
ባለፉት አምስት ዓመታት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባከናወናቸው መጠነ ሰፊና ስር ነቀል የመሰረተ ልማት እና የአገልግሎት ማሻሻያ ስራዎች ለከተማዋ የላቀ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት እያተረፈላት ይገኛል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባቀረቡት የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጸጸም ሪፖርት እንደገለጹት፣ አዲስ አበባን ወደ ስሉጥ ከተማነት ለመቀየር እየተደረገ ባለው ተከታታይ ጥረት በርካታ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችንና እውቅናዎችን ለመቀዳጀት ችላለች።
እ.ኤ.አ 2024 በደቡብ ኮሪያ የተበረከተውና ለከተማዋ ከፍተኛ አመራር እውቅና የሰጠው የ”ሴኡል ስማርት ከተማ ሽልማት” የአዲስ አበባን የቴክኖሎጂና ዘመናዊ አሰራር ሽግግር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያረጋገጠ ትልቅ ስኬት ነው።

ይህ ሽልማት ከተማዋ ነዋሪዎቿን ተጠቃሚ ያደረጉ ዲጂታል አሰራሮችን በመዘርጋቷና ዘመናዊ መፍትሄዎችን በመተግበሯ ነው የተበረከተላት።
በናይሮቢ ኬንያ በተካሄደው የአፍሪካ ስማርት ከተሞች ኢንቨስትመንት ሰሚት ላይ አዲስ አበባ “የአፍሪካ ምርጥ ስማርት ከተማ ሽልማት (እ.ኤ.አ 2024)” ባለቤት ለመሆን መብቃቷ ይታወሳል። ይህም ከተማዋ በአህጉሪቱ ካሉ ግንባር ቀደም መዲናዎች ጋር በቀዳሚነት ያስጠቅሳታል።
ከስሉጥ ከተማ ግንባታ ባሻገር ፣ በመሰረተ ልማትና በማህበራዊ ዘርፍ የተመዘገቡት ስኬቶችም ዓለም አቀፍ ትኩረቶችን መሳብ ችለዋል።

ከተማዋ ለተማሪዎችና ለዝቅተኛው ማህበረሰብ ክፍል በዘረጋችው የተሳካ የምገባ ስርዓት በብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሪዮ ከተማ “የምገባ ፕሮግራም ሽልማት” የተበረከተላት ሲሆን፣ ይህም በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በማደግ ላይ ላሉ ከተሞች በአርአያነት የሚጠቀስ ተግባር ሆኗል።
ለቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት መሻሻል በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ የተሰጠው እውቅና “የC40 ከተሞች የብሉምበርግ ሽልማት” ከተማዋ በአካባቢ ጥበቃ ረገድ የወሰደችውን ቁርጠኝነት ያሳያል። በመንገድ ደህንነትና ፍጥነት ማስተዳደር ላይ ባስመዘገበችው ውጤትም የዓለም አቀፍ የመንገድ ደህንነት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች።

እነዚህ ዓለም አቀፍ እውቅናዎች የከተማዋን የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ይበልጥ የሚያጎሉ ናቸው። በተጨማሪም ሽልማቶቹና እውቅናዎቹ አዲስ አበባ ለመኖርና ለመጎብኘት ምቹና ንፁህ ከሆኑ ጥቂት የአፍሪካ ከተሞች ተርታ ለማሰለፍ የተጀመረውን ጉዞ በእጅጉ እንደሚያፋጥኑት ይታመናል።
በታደሠ ሽፈራው