AMN – ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም
በረጲ(ቆሼ) የሚከናወነው የችግኝ ተከላ ለአካባቢው ጽዳት ብቻ ሳይሆን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ (ዶ/ር) ፣ በከባድ ሽታ የሚታወቀው የረጲ(ቆሼ) ቆሻሻ ማከማቻ ስፍራ አሁን ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሽታውን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በረጲ እየተከናወነ ያለው አረንጓዴ ልማትም ነገ ስፍራው ንጹሕና ጽዱ ሆኖ ፣ ሰዎች የሚዝናኑበትና ሐሳብ የሚለዋወጡበት እንዲሆን የሚያስችል መሆንኑንም ጠቁመዋል።

በም/ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ፣ በሥፍራው የሚከናወነው የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል።
ቀድሞ በቦታው ላይ ለተወሰኑ ሰከንዶች እንኳን ቆሞ ለመንቀሳቀስ እጅግ አስቸጋሪ እና ለመተንፈሻ አካል በሽታዎች የሚያጋልጥ የነበረ መሆኑን ያስታወሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ አሁን ላይ ግን አካባቢው ታጥሮና ውስጡ ለእንቅስቃሴ ምቹ ሆኖ እየተለወጠ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ደሲሳ ፤ የከተማ አስተዳደሩ ስሉጥ ከተማን ለመገንባትና ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝን ተግባራዊ ለማድረግ ከሚሠራቸው ቁልፍ ተግባራት መካከል የረጲ ቆሻሻ ማከማቻ አስተዳደር አንዱ መሆኑንና ይህም የጽዳት ብቻ ሳይሆን የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በሥፍራው የአፈር መንሸራተትን ለመከላከል የሚደረገው ጥረትና አሁን በቦታው ላይ የታየው ለውጥ እጅግ የሚያስደስት መሆኑን ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ አክለውም፤ ከዚህ ቀደም በአካባቢው የተከሏቸው ችግኞች መጽደቃቸውንና በባለቤትነት ስሜት እየተንከባከቡ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በወርቅነህ አቢዮ