ከውይይት ወደ መተማመን የሚያሻግርው የመግባቢያ ድልድይ-የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ

You are currently viewing ከውይይት ወደ መተማመን የሚያሻግርው የመግባቢያ ድልድይ-የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ

AMN – ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የተለያዩ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በአንድነት የሚኖሩባት ሀገር ብትሆንም፣ በታሪካዊ ጠባሳዎች፣ በልዩነቶች እና ባለመግባባቶች የተፈጠሩ ክፍተቶች የቁርሾ መነሾ ሆነው ቆይተዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ እነኚህን ክፍተቶች የሚያጠብ ፣ የሀሳብ ልዩነቶችን የሚያቀራርብ እና የጋራ የሀገር ግንባታ ራዕይ የሚፈነጥቅ ታላቅ ተስፋ ሆኖ ብቅ ብሏል።

ሀገራዊ ምክክሩ እንደሌሎች ተለምዷዊ የውይይት መድረኮች ብቻ አይደለም። ይህ መድረክ ከተለያየ የሀገሪቱ ክፍል የተውጣጡ አባቶች፣ እናቶች፣ ወጣቶች፣ ምሁራን እና የህብረተሰብ ክፍሎች በጋራ የሚቀመጡበት፣ ያለፈውን ህመም በአንድነት የሚፈውሱበት እና የወደፊቱን የጋራ መንገድ የሚነድፉበት የመግባባት ድልድይ ነው።

ምክክሩ የጋራ እሴቶችን በማጎልበት ፣ ልዩነቶቻችንን እንደ ጥንካሬ የምንጠቀምበትን መንገድ በመፈለግ፣ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ አብሮ የመኖርን እሴት ያጠነክራል።

የታሪክ ትርክትን በማስታረቅ ተቃራኒ የሚመስሉ ታሪካዊ ትርክቶችን በማስታረቅ ፣ ለጋራ ብሔራዊ ማንነት እውቅና የሚሰጥ ሥርዓት ለመዘርጋት ምቹ መደላድል ይፈጥራል።

የተፈጠረውን የመጠራጠር መንፈስ በውይይት በማስወገድ፣ እውነተኛ የሆነ የወንድማማችነት ስሜትን በመገንባት መተማመን ለመገንባትም ያስችላል።

ማህበረሰቦች ሲቀራረቡ ለሀገር የሚፈጠረው ፋይዳ እጅግ የላቀ ነው። ከምክክሩ የሚመነጨው መተማመን ለሰላም፣ ሰላም ለልማት፣ ልማት ደግሞ ለጋራ ብልጽግና ይበጃል። ሀገራዊ ምክክሩ በልዩነቶች መካከከል ያለውን ውጥረት በማርገብ፣ ህዝቡ በጋራ ችግሮቹ ላይ በሰከነ መንፈስ እንዲወያይ በማድረግ ለዘላቂ ሰላም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

ሀገራዊ ምክክሩ የልዩነት ማጥፊያ፣ የአንድነት ማጠናከሪያ እና የሰላም መሰረት ሆኖ ያገለግላል።

ይህ መድረክ የኢትዮጵያን “በአንድነት መተሳሰር” ህልም ወደ ተጨባጭ እውነታ የሚቀይር የጋራ ጉዞ ነው። ሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ተወካዮች በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ በቅንነት እና በጋራ ፍቅር በመሳተፍ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የምትሻል ኢትዮጵያን ለማውረስ ይመክራሉ፡፡

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review