AMN- ሐምሌ 11/2018 ዓ.ም

23ኛው የዓለም ዋንጫ ሊጠናቀቅ ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ይቀሩታል። ዛሬ ለሊት የሚከናወነው የደረጃ እንዲሁም ነገ የሚደረገው የፍፃሜ ጨዋታዎች የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ መገባደድን ያበስራሉ።
የደረጃ ጨዋታው ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች ለመጫወት የሚጓጉለት አይደለም። የእንግሊዙ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል “የእኛም ይሁን የፈረንሳይ ተጫዋቾች የዛሬውን ጨዋታ አይፈልጉትም ፤ ፍላጎታቸው ፍፃሜውን መጫወት ነው።’’ ሲል ተናግሯል።
የፈረንሳዩ አሰልጣኝ ዲዲዬ ዴሾም ቢሆን ለጨዋታው ጉጉት የለውም። “ የፈለግነው ወይም የተጠበቅነው ቦታ አልተገኘንም ፤ ነገር ግን እውነታውን መቀበል አለብን ፤ ጨዋታውን ከማድረግ ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም።“ ብሏል።
ጨዋታው በደጋፊዎች ዘንድም ብዙ ትኩረት አይሰጠውም። ፊፋ ዛሬ ጨዋታ የሚከናወንበት ሚያሚ ስታዲየም የመግቢያ ትኬት ለመሸጥ ተቸግሮ ታይቷል።
አንዳንዶች ጨዋታውን እንደወዳጅነት ፣ ሌሎች ደግሞ ከዚህም አውርደው የገቢ ማሰባሰቢያ ጨዋታ አድርገው ይመለከቱታል። ለፊፋ ግን ይፋዊ ጨዋታ ነው።
አሸናፊው ቡድን የነሐስ ሜዳልያ ያገኛል። የበለጠ የሽልማት ገንዘብም ወደ ካዝናው ያስገባል። ዘንድሮ 3ኛ ደረጃ ይዞ ሚያጠናቅቀው ብሔራዊ ቡድን 29 ሚሊየን ዶላር ሲበረከትለት ፤ ተሸናፊው 27 ሚሊየን ዶላር ያገኛል።
ፊፋ በተለይ በታላላቅ ብሔራዊ ቡድኖች ብዙ ባይፈለግም የደረጃ ጨዋታን ሳያከናውን የቀረው በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ነው። በመጀመሪያው የ1930 እንዲሁም የ1950 የዓለም ዋንጫዎች ላይ ብቻ ነው ያልተካሄደው። ከዚህ ውጪ 20 ጊዜ መከናወን ችሏል።
ጨዋታው ይፋዊ ስለሆነ ክብረወሰኖች ይመዘገባሉ። ከዚህ ቀደም ፈረንሳዊው ተጫዋች ጀስት ፎንቴን በ1958 ሀገሩ ምዕራብ ጀርመንን በደረጃ ጨዋታ 6ለ3 ስታሸንፍ አራት ግብ አስቆጥሮ ነበር። በአንድ ጨዋታ ይህን ያህል ግብ ያስመዘገበ ብቸኛው ተጫዋች ሆኗል።
በ2002 ቱርኪዬ ደቡብ ኮሪያን 3ለ2 ስታሸንፍ የቱርኪዬ ተጫዋች ሀካን ሱከር ጨዋታው በጀመረ በ11 ሰከንድ ግብ አስቆጥሯል። ይህም የዓለም ዋንጫው ፈጣኑ ግብ ተብሎ በታሪክ መዝገብ ሰፍሯል።
ቡድኖች በመጠኑ ከጫና ተላቀው ስለሚጫወቱ በደረጃ ጨዋታዎች በርካታ ግቦች ይቆጠራሉ ፤ እስካሁን በ20 የደረጃ ጨዋታዎች 76 ግቦች መረብ ላይ አርፈዋል። በጨዋታ በአማካይ 3.8 ግቦች ይመዘገባሉ ማለት ነው።
ይህ ለኪሊያን ምባፔ ፣ ሀሪ ኬን እና ጁድ ቤሊንግሃም ጥሩ አጋጣሚ ይመስላል። ምባፔ ከሊዮኔል ሜሲ ጋር እኩል ስምንት ግብ አስቆጥሮ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ለመጨረስ እየጣረ ይገኛል።
የ27 ዓመቱ የማድሪድ ተጫዋች በአጠቃላይ 20 የዓለም ዋንጫ ግቦቹን ለማሳደግም ትልቅ አጋጣሚ ይፈጥርለታል። በዚህም ሚበለጠው 21 ግብ ባለው ሊዮኔል ሜሲ ብቻ ነው። ሀሪ ኬን እና ጁድ ቤሊንግሃምም እያንዳንዳቸው ስድስት ግቦች አስቆጥረዋል።
ፈረንሳይ እና እንግሊዝ በዓለም ዋንጫ ሲገናኙ የዛሬው ለአራተኛ ጊዜ ነው። እንግሊዝ ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናት ፣ ፈረንሳይ አንድ ጊዜ አሸንፋለች።
ቬንዙኤላዊው ዋና ዳኛ ጄሱስ ቫሌንዙኤላ በዋና ዳኝነት የሚመሩት የዛሬ ጨዋታ ለሊት 6፡00 ላይ በማያሚ ስታዲየም ይከናወናል።
በሸዋንግዛው ግርማ
See less