የልማት ሥራዎችን ከሰው ተኮር ተግባራት ጋር በማስተሳሰር የተሠራው ሥራ ስኬታማ ሆኗል

AMN — ሐምሌ 11/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለውን ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ተከትሎ የነዋሪዎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን ከሰው ተኮር ሥራዎች ጋር በማሰናሰል በመሠራቱ ስኬት መመዝገቡን የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታረቀኝ ወርቅነህ ገለጹ፡፡

ክፍለ ከተማው ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚስተናገድበት እንደመሆኑ ለነዋሪውም ሆነ ለንግዱ ማኅበረሰብ ምቹና ውብ የማድረግ ተግባራት ባለፉት አምስት ዓመታትና በተያዘው በጀት ዓመት መከናወናቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በተለይም በእሳት አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት በነበረው የቅጠል ተራ አካባቢ በከንቲባ አዳነች አቤቤ የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ እየተገነባ ያለው ግዙፍ የመኖሪያና የንግድ መንደር ግንባታ በቅርቡ ተጠናቆ ለተጎጂዎች እንደሚተላለፍ ጠቁመዋል።

ይህ መንደር ከ6 መቶ በላይ አባወራዎችን የሚይዝ፣ የልጆች መጫወቻ፣ የስፖርት ማዘውተሪያና የንግድ ሱቆችን ያካተተ በመሆኑ የአካባቢውን ገፅታ ሙሉ በሙሉ እንደሚቀይረው ገልጸዋል።

በክፍለ ከተማው ካሉት 711 ብሎኮች መካከል 460 ያህሉ ‘ሞዴል መንደር’ ሆነው መለየታቸውን ጠቅሰው፤ ለእነዚህ መንደሮች የደኅንነት ካሜራዎች፣ ሙሉ የሌሊት መብራትና የፅዳት መሠረተ ልማት እንደተሟላላቸው አረጋግጠዋል።

በመርካቶ የመንገድ ላይ ንግድን ሥርዓት ለማስያዝ በመንገድ ላይ ያለአግባብ ይነግዱ የነበሩ ከ4 ሺህ 9 መቶ በላይ ዜጎች ተለይተው ዐቅም ያላቸው በሕግ እንዲስተናገዱ ሲደረግ፤ አነስተኛ ዐቅም ያላቸው በኮሪደር ንግድ እንዲደራጁ ተደርጓል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ለ50 ዓመታት ሳይጠገን የቆየው የእህል በረንዳ በነጋዴውና በሕዝብ አጋርነት በከፍተኛ ሁኔታ እየታደሠና እየዘመነ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

እነዚህን የልማት ሥራዎች ከሰው ተኮር ተግባራት ጋር አጣጥሞ ማስኬድ በመቻሉ ስኬት መመዝገቡንም ለኤ ኤም ኤን ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ብቻ ከ60 ሺህ በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ የምግብ አቅርቦትና የትምህርት ቁሳቁስ እንደተሟላላቸውም አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል 667 የአረጋውያንና ዐቅመ ደካሞች ቤቶች ሙሉ በሙሉ ታድሰው ርክክብ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

እናቶች በነጻነት እንዲሠሩ የሚያስችሉ የሕጻናት ማቆያ ማዕከላት፣ ለወጣቶች ሁለንተናዊ ስብዕና ግንባታ የሚጠቅሙ የስፖርት ሜዳዎች እንዲሁም ዘመናዊ የንባብ ማዕከላትና የባህል አዳራሾች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውንም አብራርተዋል፡፡

በወርቅነህ አብዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review