AMN- ጳጉሜን 05/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሞጆ ከተማ የተገነባዉን እና በዓመት እስከ 1 ሚሊዮን ባለ 20 ጫማ ኮንቴነሮችን የማስተናገድ አቅም ያለዉን ግዙፍ ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፍያን መርቀዋል፡፡
ማዕከሉ በመጀመሪያዉ ምዕራፍ በ60 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባ ሲሆን ደረቅ ብትን ጭነቶችን በሀገር ውስጥ ለማሸግ ከማስቻሉም በላይ የውጭ ምንዛሬን በመቆጠብ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድልን የሚፈጥር ነዉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ማዕከሉ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስኬት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡

የማዕከሉን የአሰራር ፍጥነት ለማሳደግ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተተከለው የባቡር ላይ ክሬን ከባቡር መስመር የሚደረገውን የኮንቴነር ዝውውር በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚያከናዉንም ጨምረዉ ገልጸዋል፡፡
ሙሉ አሰራሩ በዘመናዊ ዲጂታል መሰረተ ልማት የተሳሰረ በመሆኑ፣ ለተገልጋዮች ፈጣን እና አስተማማኝ አገልግሎትን ያሳልጣል።
ማዕከሉ ከኢትዮ-ጅቡቲ መስመር ባሻገር ኢትዮጵያን፣ ደቡብ ሱዳንን እና ዩጋንዳን የሚያስተሳስረው የ‘ደሱ’ ኮሪደር አካል መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማዕከሉ ምረቃ ወቅት ተናግረዋል፡፡

በሞጆ ከተማ የተገነባዉ ግዙፉና ዘመናዊዉ የሎጂስቲክስ ማዕከል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ደረጃ ላይ ያላትን ስፍራ የሚያሻሽልና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግር ትልቅ ድል ነው።
በወንድማገኝ አሰፋ