እኛ የትግራይ ክልል ወጣቶች ሰላምና ልማት እንጂ የሕገ-ወጡን ሕወሓት ቡድን የጦርነት ዳንኪራ አንፈልግም

AMN – ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም

የትግራይ ክልል ወጣትና ህዝብ ጽኑ ሰላምና ልማት እንጂ የሕገ-ወጡን የሕወሓት ቡድን የጦርነት ዳንኪራ እንደማይፈልግ የሕገ-ወጡን ቡድን አፈሳና አፈና ሸሽተው አዲስ አበባ የመጡ ወጣቶች ገለጹ።

በትግራይ የሰላምና ለውጥ ምክር ቤት አስተባባሪነት ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን አፈሳና አፈና በመቃወም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።

”አፈሳ ይቁም፤ ሰላም ይስፈን” በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ የክልሉ ተወላጆች፣ግፍን በመሸሽ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ወጣቶች፣ የሲቪክ ማህበራትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

አፈሳና አፈናውን በመሸሽ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ወጣቶች እንደተናገሩት፤ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የክልሉን ወጣቶች በግዳጅ በማፈስ ወደ ጦር ካምፖች እያጋዛቸው ይገኛል።

ሕገ-ወጥ ቡድኑም የክልሉን ወጣቶች ለሱዳንና ሻቢያ የጥፋት ኃይሎች በመሸጥ ሰብዓዊ ክብርን የሚጋፋ ኢ-ሰብዓዊ ግፍ እየፈጸመ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት ሶሎሞን እምባዬ፤ ጦርነት ናፋቂው ሕገ-ወጥ ቡድን ካለፈው ስህተቱ ሳይማር ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ገልጿል።

የጦርነት ነጋዴው ሕገ-ወጥ ቡድን ፅምዶ በተሰኘ የጥፋት ጥምረት ወጣቶችን ከየቤተ-ዕምነቱ፣ ከገበያና ከየመንገዱ ለቅሞ በመውሰድና ለውጭ ገበያ ጭምር በመሸጥ እናቶችን እያስለቀሰ መሆኑን ተናግሯል።

የትግራይ ሕዝብ ፍላጎት ጽኑ ሰላምና ልማት ብቻ መሆኑን ያነሳው ወጣቱ፤ እናቶችም የጦር መሳሪያ ካነገበው ኃይል ጋር በመጋፈጥ ተቃውሟቸውን እያሰሙ መሆናቸውን አክሏል።

ሕገ-ወጥ ቡድኑ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በማፍረስ ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ጋር በፈጠረው የጥፋት ጥምረት በሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና መከራ የፌዴራል መንግሥት እንዲያስቆም ጥሪ አቅርቧል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት እምሩ ብርሃኑ በበኩሉ፤ ሕገ-ወጡ ቡድን ወጣቶችን ለውጭ ኃይሎች በመሸጥ የገቢ ምንጭ ማድረጉ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ መሰነባበቱን ገልጿል።

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የትግራይ ክልል ወጣቶችና ሕዝብም የቡድኑን የጦርነት ጉሰማ በመታገል ሰላም ፈላጊነታቸውን በተግባር ሊያሳዩ እንደሚገባ አሳስቧል።

ወጣት መብራህቱ ኻልአዩ በበኩሉ፤ ቡድኑ በክልሉ የከፈተው የአፈሳና የአፈና ጭቆና ሕዝብን ለስቃይ፣ወጣቶችን ደግሞ ለስደት መዳረጉን ጠቁሟል።

አክሎም፥ ቡድኑ ወጣቶችን በማፈን ከሚፈፅመው ግፍ በተጨማሪም አርሶ አደሩ የእርሻ ሥራውን በአግባቡ እንዳያከናውን ተጽዕኖ እየፈጠረ መሆኑን መናገሩን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review