AMN ጳጉሜን 2/2018

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና ዋና ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በሴኡል ደቡብ ኮሪያ በመካሄድ ላይ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች (ICDPP) የምክክር መድረክ ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ይህ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክክር (ICDPP) ከኤሺያ፣ ከአፍሪካ፣ ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ የተወጣጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መሪዎችን የሚያገናኝ መድረክ ነው።

የመድረኩ ዋነኛ ዓላማ በልዩ ልዩ የፖለቲካ ባህሎች መካከል የእርስ በእርስ ግንዛቤን ማሳደግ፣ እምነትን ማጠናከር፣ በጋራ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ መለዋወጥ እና ቀጣይነት ያለው አለም አቀፍ ትብብር የሚደረግባቸውን መንገዶችን ማመላከት ነው።
በመድረኩ እየተሳተፉ የሚገኙት የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ፣ የምክክር መድረኩ ሊኖረው ስለሚገባው ተልዕኮ በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዲፕሎማሲ ሚና፣ አወቃቀር፣ ሊከተላቸው የሚገቡ መርሆዎች እና በብልፅግና ፓርቲ የመደመር እሳቤ ተሞክሮዎች ዙሪያ ንግግር አድርገዋል።

አቶ አደም በንግግራቸው፣ የምክክር መድረኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብን ፍላጎት የሚያንፀባርቁ መሪዎችን የሚያፈሩና ፖሊሲዎችን የሚቀርፁ መሆናቸውን ታሳቢ ማድረግ እንዳለበት አንስተዋል።
መድረኩም በመንግስታት መደበኛ ዲፕሎማሲ እና በሕዝቦች መካከል ባለው ግንኙነት መካከል ያለውን ክፍተት የሚሞላ ወሳኝ የጋራ መድረክ ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል።
በተለይም ዋና ትኩረቱ እምነትን መገንባት፣ የርዕዮተ-ዓለም ውጥረትን መቀነስ፣ ተቋማዊ ልምድ ልውውጥን ማጠናከር፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው መሪዎች ማፍራት ላይ መተባበር፣ ግጭቶችን መከላከል እና ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር መሆን እንዳለበት አብራርተዋል።
በተጨማሪም የሃሳብ ብዝሃነት፣ ሉዓላዊነት፣ እኩልነት፣ አካታችነት፣ ተቋማዊነት እና ተጨባጭ ትብብር መርሆዎች ሊመራ እንደሚገባም አክለዋል።
የምክክር መድረኩ በዋናነት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸውም ዋና ዋና ጉዳዮች ሶስት መሆናቸውንም አንስተዋል።
የመጀመሪያው ዲሞክራሲያዊና ተቋማዊ ጥንካሬ ማረጋገጥ ሲሆን በዚህም ሰላማዊ ምርጫን፣ የህግ የበላይነትን እና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ማተኮር አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
ሁለተኛው አካታች ልማትና ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን ማምጣት ሲሆን ከዚህ አኳያ ብልፅግና ፓርቲ የሚመራበት የመደመር እሳቤ መሰረት በማድረግ፣ ሁሉንም አቅሞች ተጨማሪ እሴትና አቅም በሚፈጥር አኳኃን ደምሮ በመጠቀም በማጎልበት የምግብ ሉዓላዊነትን፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እና ዘርፈ ብዙ ምርታማነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል አንስተዋል።
ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል በሶስተኛነት ያነሱት ሰላም ግንባታና ቅድመ-ግጭት መከላከልን ማጠናከር ሲሆን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግጭትንና ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ለመከላከል የሚያስችሉ ምክክሮች ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ገልፀዋል።
በአጠቃለይ አቶ አደም፣ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክር መድረክ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች መርህን መሰረት ያደረገና በተግባር ላይ ያተኮረ ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ካስቻለ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት፣ የጋራ ብልፅግና፣ ፍትህና ርትዕ የተረጋገጠበት ዓለም ለመፍጠር አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት እምነታቸው መሆኑን ማንሳታቸዉን ከብልጽግና ፖርቲ ጽ/ቤት ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።
See less