በፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት ልዑክ ዱባይ ገባ

You are currently viewing በፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት ልዑክ ዱባይ ገባ

AMN- ጳጉሜን 1/2018 ዓ.ም

በኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት ልዑክ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ጉባኤ (AIM Congress) ላይ ለመሳተፍ ዱባይ ገብቷል።

በፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የተመራው ልዑክ ዱባይ ሲደርስ በአገሪቷ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጐላቸዋል።

የኢንቨስትመንት ጉባኤው ከነገ ጳጉሜን 2 እስከ 4 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት በዱባይ ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል ይካሄዳል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2011 የተቋቋመው ይህ የኢንቨስትመንት ጉባዔ ውጤታማ የኢንቨስትመንት የማስተዋወቂያ ስትራቴጂዎችን በማሳደግና ለኢኮኖሚ ምርታማነት እድሎችን በማመቻቸት የዓለምን ኢኮኖሚ ለማጎልበት የሚሰራ የኤም ግሎባል ፋውንዴሽን ኢንሼቲቭ ነው።

በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት፣ በሀገራት መካከል አጋርነትና የኢከኖሚ ትብብርን በማጠናከር እንዲሁም በመስኩ የሚስተዋሉ ችግሮችን እልባት በመስጠት በመካከለኛው ምስራቅ ዋነኛ የኢንቨስትመንት መድረክም ሆኖ እያገለገለ ነው።

በጉባኤው የአገራት መሪዎች፣ በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ ግዙፍ የቢዝነስና ተቋማት ሥራ አስፈጻሚዎች፣ፖሊሲ አውጪዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ተወካዮች፣ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በመድረኩ በጋራ ይመክሩበታል።

በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚሁ የዱባይ ጉባኤ ታዳሚዎች በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በዘላቂ ልማትና በስትራቴጂያዊ አጋርነት ላይ ትኩረት አድርገው ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ይህንንም ተከትሎ መድረኩ የዓለምን ኢኮኖሚ ለማጠናከር የሚያስችሉ ውጤታማ ውይይቶችና ግዙፍ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች እንደሚያደረጉ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል።

ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በተለይም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሣብና የኢኮኖሚ ትብብሮችን በማጠናከር የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ለማሣደግና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ እየሠራች እንደምትገኝ ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review