ተመሳሳይ በጀት ተመድቦ በአፈጻጸም መራራቅ የሚያስጠይቅ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing ተመሳሳይ በጀት ተመድቦ በአፈጻጸም መራራቅ የሚያስጠይቅ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ሐምሌ 13/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ ተቋማት ውስጥ ተመሳሳይ መዋቅር፣ በጀትና የሰው ኃይል ተመድቦ፣ በአፈጻጸም እና በውጤታማነት ላይ ሰፊ መራራቅ እንደሚታይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ ይህንን ያሉት የከተማ አስተዳደሩ የ2018 በጀት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ ነው።

አመራሩ ዘንድ በሚታዩ የሪፖርት ግድፈቶችና የመረጃ አያያዝ ክፍተቶች ላይ ጠንከር ያለ ትችት የሰነዘሩት ከንቲባዋ፣ ስህተትን አምኖ በወቅቱ ማስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከንቲባዋ አያይዘውም፣ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ማቅረብ ከሌብነት ጋር በተመሳሳይ ደረጃ የሚያስጠይቅ ነው ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

የወደፊት ሪፖርቶች በሕዝቡ ሕይወት ላይ ያመጡትን ሁለንተናዊ ለውጥና ጥቅም በግልጽ ማሳየት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በኮሪደር ልማት አካባቢዎች ሕብረተሰቡ ቆሻሻ ከመጣል እየተቆጠበ የመጣ ቢሆንም፣ የፅዳት ሥራን የእያንዳንዱ ነዋሪ የዕለት ተዕለት ባህል ማድረግና እያንዳንዱ ሰው ደጃፉን በባለቤትነት ማጽዳት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በተያያዘም ምርታማነትን ማሳደግና አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን በመጨመር የኑሮ ውድነት ጫናን የመከላከል ሥራ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቤት ልማት ፕሮግራሞች ያረጁ የከተማ ክፍሎችን የማደስ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትም በቀጣይ የማኅበረሰቡን ጥያቄዎች በግልጽ በማንሳት ሚዛኑን የጠበቀ መረጃ ለሕዝብ ማድረስ እንዳለበት አሳስበዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ለቤት፣ ለትራንስፖርት፣ ለውሃ፣ ለመንገድ እና ለፍሳሽ ማስወገጃ መሠረተ ልማቶች ከፍተኛ በጀት መመደቡን ያስታወሱት ከንቲባዋ፣ ለተመዘገቡት ስኬቶች የሕዝብና የልማት አጋሮች ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸው በቀጣይም ይህ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review